Go to full page →

የሥራ ጥቅም CLAmh 100

ሥራ የመላ አካላችን ደንብና ሥርዓት ነው፡፡ እያንዳንዱ የአካል ክፍል የየግል ሥራ ስላለው የተመደበለትን ሥራ በሚገባ ሲሠራ እድገቱና ብርታቱ የተሟላ ይሆናል፡፡ የአካላት ክፍሎች መደበኛ ሥራቸውን ሲያከናውኑ ኃይልና ብርታት ያገኛሉ፤ ግን ሲቦዝኑ (ካልሠሩ) መድከምና ከአገልግሎት ውጭ የመሆን ዕድል ይጠብቃቸዋል፡፡ አንድ ክንዳችሁን ለጥቂት ሣምንታት አሥራችሁ ብትፈቱት ስትሠሩበት ከነበረው እጃችሁ ይልቅ ሰንፎ ታገኙታላችሁ፡፡ ሥራ ፈትነት በጠቅላላው በአካል ክፍሎችን ላይ የዚህኑ ዓይነት ስንፍና ያስከትላል፡፡ CLAmh 100.1

ስንፍና የሕመም ዋናው ምንጭ ነው፡፡ ሥራ የደምን መዘዋወር ያፋጥነዋል፤ ያስተካክለዋልም፡፡ ስንፍና ግን ደምን በሚገባ እንዳይዘዋወር ካለማድረጉም በላይ ለጤና ተስማሚ የሆነውን የደምን መለዋወጥ አያስገኝም፡፡ በሰውነት እቅስቃሴ አማካይነት ሊወገዱ የሚችሉት የአካል ውስጥ ቆሻሻዎች እንዳሉ ይቀመጣሉ፡፡ ቆዳ ጤነኛ አይሆንም፤ ሳንባዎች ንጹህ አያር አያገኙም፡፡ የአካላችን ይዞታ በቆሻሻ አጣሪው ክፍል ላይ ተጨማሪ ሥራ ስለሚያስከትልበት ትርፉ በሽታ ነው፡፡ CLAmh 100.2

አንዳንድ ጊዜ የዕረፍት ተፈላጊነት መናቅ የለበትም፡፡ ማንኛውንም የሥራ ዓይነት ከመጠን በላይ በመሥራት ድካም ሲከተል ለጥቂት ጊዜ ሙሉ ዕረፍት ማድረግ ከአደገኛ በሽታ ሊያድን ይችላል፡፤ግን በስንፍና ምክንያት የሥራን ጊዜ ማባከን አይበጅም፡፡ CLAmh 100.3

በአእምሮ ሥራ ምክንያት ጤናቸው የተበደለ ሰዎች ከአድካሚ አሳብ መከልከል ቢኖርባቸውም አዕምሮን በሥራ ላይ ማዋልን እንደ አደገኛ ነገር አድርገው መመልከት የለባቸውም፡፡ CLAmh 100.4

ብዙዎች የጤና ይዞታቸውን ከሆነው የባሰ አድርገው የሚመለከቱ አሉ፡፡ የዚህ ዓይነት አስተሳሰብ ከሕመም ለመዳን እንቅፋት ስለሆነ ሊወገድ ይገባዋል፡፡ CLAmh 100.5

ወንጌላውያን፣ መምህራን፣ ተማሮችና ሌሎችም የአእምሮ ሥራ የሚሰሩ ሰዎች የአካል ሥራ ስለማይሠሩ ከበሽታ ላይ ይወድቃሉ፡፡ የዚህ ዓይነት ሰዎች የሚያስፈልጋቸው አካላቸውን በሥራ ላይ ማዋል ነው፡፡ CLAmh 101.1

የምግብን ይዞታ መቈጣጠር፣ የተስተካከለ አካል ማጠንከሪያ ልምምድ ሲታከልበት አካልንና የአእምሮን ብርታት ያስገኛል፡፡ የጭንቅላት ሥራ ላለባቸው ሰዎች ጉልበት ይጨምርላቸዋል፡፡ CLAmh 101.2

ብርታታቸው የተዳከመባቸው ሰዎች ጉልበት ሥራ መሥራት አያስፈራቸው፡፡ ግን ሥራ ውጤት እንዲያስገኝ ከተፈለገ ተስማሚና በሥርዓት የሚመራ ይሁን፡፡ የቤት ውጭ ሥራ (ሽርሽር) ከሁሉም የበለጠ ነው፡፡ የደከሙትን የአካል ክፍሎች እንዲያጠነክር ሆኖ መዘጋጀት ይገባዋል፡፡ CLAmh 101.3

ደግሞ ከልብ መሠራት አለበት፡፤ የእጅ ሥራዎች አሰልችዎች መሆን የለባቸውም፡፡ ደካማዎች ፈጽሞ ሥራ ፈት ሲሆኑ ስለራሳቸው ማሰብ ስለሚያበዙ ብስጩና ቁጡዎች ይሆናሉ፡፡ ስሜታቸው ይባባስና ራሳቸውን ከእውነተኛው በታች ዝቅ አድርገው ይገምቱታል፡፡ በፍጹም አንድም ነገር ማድረግ የማይችሉ ይመስላቸዋል፡፡ CLAmh 101.4

ለዚህ ሁሉ መድህኑ ተጠንቶ በሚገባ የሚደረግ የአካል ማጠንከሪያ ልምምድ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ይህ ዘዴ የማያዳግም ፈውስ ያስገኛል፡፡ ሰው ሲሠራ ፈቃደኝነቱ ይበረታል፡፡ ድውያንም ማድረግ ያለባቸው ፈቃደኝነታቸውን ማሳየት ነው፡፡ ፈቃደኝነት ሲጠፋ አስተሳሰባችን ያልተስተካከለ ይሆናሉ፤ በሽታን መቋቋም ያቅተናል፡፡ CLAmh 101.5