Loading...
Larger font
Smaller font
Copy
Print
Contents
  • Results
  • Related
  • Featured
No results found for: "".
  • Weighted Relevancy
  • Content Sequence
  • Relevancy
  • Earliest First
  • Latest First
    Larger font
    Smaller font
    Copy
    Print
    Contents

    በሰውና በሰይጣን መካከል ያለው ጠላትነት

    በአንተና በሴቲቱ መካከል፥ በዘርህና በዘርዋም መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፥ አንተም ሰኰናውን ትቀጠቅጣለህ።» (ዘፍጥረት 3፡15)። ይህ ቃል ሰው በኃጢአት ከወደቀ በኋላ በሰይጣን ላይ የተላለፈው መለኮታዊ ፍርድ ከመሆኑም በተጨማሪ እስከ ዘመን ፍጻሜ ድረሰ ያለውን ጊዜ አጠቃሎ የሚይዝና በምድር ላይ የሚኖር የሰው ዘር በሙሉ ሊያልፍ ያለበትን ታላቅ ተጋድሎ የሚያመላክት ትንቢት ነበር።ታተ 10.1

    እግዚአብሔር «ጠላትነትን አደርጋለሁ!» በማለት አስረግጦ ተናገረ። ይህ ጠላትነት በተፈጥሮ ወይም በራሱ ጊዜ የሚከሰት አይደለም። ሰው የመለኮትን ህግ እንደጣሰ ተፈጥሮው ክፉ ሆነ፤ ከሰይጣንም ጋር በአንድ ተስማማ። በኃጢአተኛ ሰውና በኃጢአት ጠንሳሽ መካከል ምንም አይነት ተፈጥሮአዊ የሆነ ጠላትነት የለም። ሁለቱም ክህደትን በመምረጥ ክፉ ሆነዋል። ከሃዲውም ሌሎች ፈለጉን እንዲከተሉ በመገፋፋት መጽናኛ እና ድጋፍ እስካላገኘ ድረስ ፍጹም እረፍት አይኖረውም። በዚህም ምክንያት የወደቁት መላእክት እና ኃጢአን ተስፋ-የለሽ ሽርክናን ይይዛሉ። እግዚአብሔር ጣልቃ ባይገባ ኖሮ ሰይጣን እና ሰው በሰማይ ላይ በማመፅ ግንባር ይፈጥሩ ነበር። ይህም ቢሳካ የሰው ዘር በአጠቃላይ በሰይጣን ላይ ጠላትነትን ከማዳበር ይልቅ በእግዚአብሔር ላይ በተቃውሞ በተነሳ ነበር።ታተ 10.2

    ቅዱሳን መላእክት በአምላክ ላይ እንዲያምጹ ያደረገው ሰይጣን እንዲሁ ሰውን እርሱ ከሰማይ ጋር በሚያደርገው ውጊያ አጋር ሊያደርገው በማሰብ ኃጢአት እንዲሰራ ተፈታተነው። በክርስቶስ ላይ ካላቸው ጥላቻ አንጻር በሰይጣንና በወደቁት መላእክት መካከል አንዳችም ልዩነት አልነበረም። በተቀሩት በሁሉም ነጥቦች ላይ አለመጣጣም ቢኖራቸውም፣ የአለማትን ገዥ ስልጣን በመቃወም ላይ ግን አጥብቀው ይስማሙ ነበር። ነገር ግን ሰይጣን በራሱና በሴቲቱ፣ በዘሩና በዘርዋ መካከል ጠላትነት እንዲኖር መደንገጉን ሲሰማ ሰብዓዊውን ተፈጥሮ የማበላሸት ጥረቱ እንደሚቋረጥና ሰውም የክፉን ኃይል መቋቋም የሚያስችለው አንዳች እርዳታ እንደሚያገኝ አወቀ።ታተ 10.3

    ሰይጣን በሰው ዘር ላይ ያለው ጥላቻ ይበልጥ የሚቀጣጠለው የሰው ልጆች በክርስቶስ አማካኝነት የእግዚአብሔርን ፍቅርና ርህራሄ ለመቀበል በመታደላቸው ነው። ሰይጣን ለሰው ልጆች ድነት የተዘጋጀውን መለኮታዊ ዕቅድ በማሰናከል ፈጣሪን ውርደት ለማከናነብ ከፍተኛ ምኞት አለው። የእግዚአብሔርን የእጁን ሥራ በማበላሸትና በማርከስ ሰማይን በጥልቅ ሀዘን፣ ምድርን ደግሞ በዋይታና በባድማነት ለመሙላት ያልማል። ይህም ሁሉ ክፋት እግዚአብሔር ሰውን ከመፍጠሩ የተነሳ የመጣ መዘዝ ነው በማለት ያመካኛል።ታተ 10.4

    ክርስቶስ በሰዎች ውስጥ የሚዘራው ጸጋ ብቻ ነው ሰው ለሰይጣን ጥላቻ እንዲኖረው የሚያስችለው። ያለዚህ ልብን የሚመልስ ጸጋ እና ህይወትን የሚያድስ ኃይል፣ የሰው ልጅ የሰይጣን ምርኮኛና የእርሱን ትዕዛዛ ለማድረግ ሁሌም ዝግጁ የሆነ ባሪያ እንደሆነ ይቀጥላል። ነገር ግን ይህ ወደ ልብ የሚገባው ጸጋ ቀድሞ ሰላም በሰፈነበት ስፍራ ግጭትን ይፈጥራል። ክርስቶሰ በሰው ልብ ውስጥ የሚዘራው ኃይል ሰው ጨካኙን እና አምባገነኑን ጠላት እንዲቋቋም ያስችለዋል። ኃጢአትን ከመውደድ ይልቅ ኃጢአትን የሚፀየፍ፣ በህይወቱ ያየለበትን የኃጢአት ስሜት የሚቋቋምና የሚያሸንፍ ማንኛውም ሰው፣ በውስጡ ከሰማይ ብቻ የሆነ አዲስ መርህ ስራ መጀመሩን ያሳያል።ታተ 10.5

    በክርስቶስ መንፈስ እና በሰይጣን መንፈስ መካከል ያለው ጥልቅ ጥላቻ ከመቼውም ይልቅ ቁልጭ ብሎ የታየው ኢየሱስ ወደዚህች ምድር በመጣ ጊዜ ነበር። አይሁዶች ኢየሱስን ያልተቀበሉበት ዋነኛው ምክንያት ኢየሱስ ምድራዊ የሆነ ሀብት ክብርና ዝና ይዞ አለመምጣቱ አልነበረም። ነገር ግን እነዚህ ውጫዊ የሆኑ ጥቅማ ጥቅሞች ከሚያስገኙት በእጅጉ የሚልቅ ኃይል መላበሱን በመመልከታቸው ነበር። የክርስቶስ ንፅህና እና ቅድስና ከማያምኑ ጠማሞች ዘንድ ጥላቻን አበቀለ። ራስን የመካድ ህይወቱና ኃጢአት አልባ ታማኝነቱ ኩፍስ እና ፍትወተኛ ለሆነው ህዝብ የዘወትር ዘለፋ ሆነ። ይህ ነበር በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ታላቅ ጥላቻን የቀሰቀሰው። ሰይጣንና ከፉ መላእክት ከክፉ ሰዎች ጋር አበሩ። የክህደት ኃይላት በሙሉ ድል አድራጊው ክርስቶስ ላይ አሴሩ።ታተ 10.6

    በክርስቶስ ላይ የተገለጸው ጠላትነት በተመሳሳይ መልኩ በተከታዮቹ ላይም ይገለጻል። የኃጢአትን አስቀያሚ ባህሪ የሚያስተውልና ከላይ በሚሰጠው ብርታት ፈተናን የሚቋቋም ማንኛውም ሰው ያለምንም ጥርጥር የሰይጣንን እና የገባሮቹን ቁጣ ይቀሰቅሳል። ኃጢአት እና ኃጢአን በዚህ ምድር እስካሉ ድረስ የእውነት መርሆች ይጠላሉ፣ ለእውነት ጥብቅና የሚቆሙ ሁሉ ደግሞ ይተቻሉ፣ ይሰደዱማል። በክርስቶስ ተከታዮች እና በሰይጣን ሎሌዎች መካከል አንዳች ሽርክና የለም። የመስቀሉ ዕንቅፋት አሁንም አላቆመም። «በእውነትም በክርስቶስ ኢየሱስ እግዚአብሔርን እየመሰሉ ሊኖሩ የሚወዱ ሁሉ ይሰደዳሉ።» (2ኛ ጢሞቴዎስ 3፡12)።ታተ 10.7

    የሰይጣን ወኪሎች በእርሱ መመሪያ ሥር ሆነው የእግዚአብሔርን መንግሥት በመቃወም የሰይጣንን ሥልጣን ለማቋቋምና ግዛቱን ለማስፋፋት ያለማቋረጥ በመስራት ላይ ይገኛሉ። ይህንንም ለማሳካት የክርስቶስን ተከታዮች ለማሳት እና ከታማኝነታቸው ለማደናቀፍ በብርቱ ይጥራሉ። እንደ መሪያቸው እነርሱም የእግዚአብሔርን ቃል በማጣመምና ትርጉሙን በማዛባት ዓላማቸውን ከግብ ለማድረስ ይሰራሉ። ሰይጣን እግዚአብሔርን ለመሳደብና ለመተቸት ጥረት እንዳደረገው ሁሉ ወኪሎቹም የእግዚአብሔርን ህዝቦች በግፍ ይነቅፋሉ። ክርስቶስን ወደ ሞት እንዲነዳ ያስገደደው መንፈስ ክፉዎች የክርስቶስን ተከታዮች እንዲያጠፉ ያነሳሳቸዋል። ይህ ሁሉ «በአንተና በሴቲቱ መካከል፥ በዘርህና በዘርዋም መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ» በሚለው በመጀመሪያው ትንቢት ቀደም ብሎ ተገልጿል። ይህም እስከ ዘመን ፍጻሜ ድረስ ይቀጥላል።ታተ 11.1

    ሰይጣን የጦር ኃይሎቹን በሙሉ አሰባስቦ ባለው አቅም ሁሉ ወደ ውጊያው ይገባል። ታዲያ የሚገዳደረው ወይም የሚገታው የጠፋው ለምንድን ነው? የክርስቶስ ወታደሮች እጅግ ዝለውና ግድ የለሽ ሆነው የሚገኙት ለምን ይሆን? ምክንያቱም ከክርስቶስ ጋር ያላቸው ትስስር የጠበቀ ስላልሆነ እና የመንፈስ ቅዱስም ሙላት ስለሚጎድላቸው ነው። እንደ ክርስቶስ ኃጢአትን አስቀያሚና ፀያፍ ነገር አድርገው አይመለከቱትም። ክርስቶስ እንዳደረገው ኃጢአትን በቁርጠኝነት አይቃወሙትም። የኃጢአትን ከልክ ያለፈ ክፋትና አደገኛነት አያስተውሉም። የጨለማውን ልዑል ባህሪ እና ኃይል እንዳይመለከቱም አይናቸው ታውሯል። የሰይጣንን ኃይል እና ተንኮል ቸል ከማለትና በክርስቶስ እና በቤተክርስቲያኑ ላይ ያሚያውጀው ጦርነት ምን ያህል ሰፊ እንደሆነ ካለማወቅ የተነሳ በሰይጣንና በስራው ላይ የሚገለጸው ጥላቻ እጅግ አነስተኛ ነው። ብዙዎች እዚህ ላይ ተታለዋል። ባላንጣቸው የክፉ መላእክትን አእምሮ የሚቆጣጠር ኃያል ጄኔራል መሆኑን ዘንግተዋል። በሳል የሆኑ እቅዶቹን ይዞ ጥበብ በተሞላበት መልኩ እየተንቀሳቀሰ ነፍሳት እንዳይድኑ ከክስርስቶስ ጋር እየተዋጋ መሆኑንም አያስተውሉም። ብዙዎች ክርስቲያን ነን ባዮች እና የወንጌል አገልጋዮችም ሳይቀሩ ስለ ሰይጣን እንደ አጋጣሚ መድረክ ላይ ቢያነሱ ነው እንጂ ሰለርሱ ሆን ብለው አስተያየት ሲሰጡና ሲወያዩ አይደመጡም። የሰይጣንን የዘወትር እንቅስቃሴ እና ስኬታማነት የሚያረጋግጡ ማስረጃዎችን ማየት ይሳናቸዋል። ስለ እርሱ ተንኮለኛነት የሚሰጡትን አያሌ ማስጠንቀቂያዎች ቸል ይላሉ። ጭራሽ ሰይጣን የሚባል መኖሩን እንኳን የረሱ ይመስላሉ።ታተ 11.2

    ሰዎች የእርሱን ዘዴዎች ባለማወቅ ሲጓዙ ጠንቃቃው ጠላት ለአፍታም ሳይተዋቸው ነቅቶ ኮቴያቸውን ይከተላል። በእያንዳንዱ የቤተሰብ አካል፣ በከተማ ጎዳናዎች፣ በቤተክርስቲያናት፣ በአገር ሸንጎዎች እና በፍትህ መድረኮች ላይ በመገኘት ግራ እያጋባ፣ እያሳተ እና በክፉ እያባበለ ወንድ፣ ሴት፣ ህፃን ሳይለይ ነፍስን እና ስጋን በመበከል፣ ቤትን በመበተን፣ ጥላቻን፣ አስመሳይነትን፣ ሁከትን፣ አመጽን እና ነፍሰ-ገዳይነትን በየስፍራው በመዝራት ላይ ይገኛል። በክርስትናው ዓለም ዘንድ ደግሞ እነዚህ ነግሮች ሊኖሩ ግድ እንደሆነ እና እግዚአብሔርም እንደፈቀደ አድርጎ የመመልከት አዝማሚያ አለ።ታተ 11.3

    ከዓለም የሚለያቸውን አጥር በማፍረስ ሰይጣን የእግዚአብሔርን ህዝቦች ለመርታት ዘወትር ይሻል። የጥንት እስራኤላውያን ወደ ኃጢአት የተሳቡት ከማያምኑት ጋር የተከለከለ ህብረትን ለመመሥረት በመድፈራቸው ነበር። የዘመኑ እስራኤላውያንም በተመሰሳይ መልኩ ወደተሳሳተ አቅጣጫ ይነዳሉ። «ለእነርሱም የእግዚአብሔር ምሳሌ የሆነ የክርስቶስ የክብሩ ወንጌል ብርሃን እንዳያበራላቸው፥ የዚህ ዓለም አምላክ የማያምኑትን አሳብ አሳወረ።» (2ኛ ቆሮንቶስ 4፡4)። ክርስቶስን በመንታ ልብ ለመከተል የሚሹ ሁሉ የሰይጣን ሎሌዎች ናቸው። ባልተለወጠ ልብ ውስጥ ኃጢአትን የማፍቀር፣ የመንከባከብና የመተግበር ብርቱ ዝንባሌ አለ። በተለወጠና በታደሰ ልብ ወስጥ ግን የኃጢአት ጥላቻ እና በኃጢአት ላይ ቆራጥ ተቃውሞ አለ። ክርስቲያኖች ከእግዚአብሔር ውጪ ከሆነውና ከማያምኑት ጋር ህብረት ሲፈጥሩ እራሳቸውን ለፈተና ያጋልጣሉ። ሰይጣንም እራሱን ከእይታ ሰውሮ በቀስታ በድብቅ ይመጣና የማሳሳቻውን ሽፋን አይናቸው ላይ ያሳርፋል። መልካም የመሰለው ምድራዊ ወዳጅነት ለጉዳት አሳልፎ እንዲሰጣቸው የታሰበ መሆኑን አያስተውሉም። እናም ከዓለም ጋር በባህሪ፣ በቃልና በተግባር መመሳሰላቸውን ሲቀጥሉ የበለጠውን እየታወሩ ይሄዳሉ።ታተ 11.4

    ከዓለም ወግና ልማድ ጋር መመሳሰል ቤተክርስቲያንን ወደ ዓለም ይስባል እንጂ ዓለምን ወደ ክርስቶስ ፈጽሞ አይስብም። ኃጢአት ሲለማመዱት አስጸያፊነቱ እየጠፋና መልካም እየመሰለ መሄዱ የማይቀር ነገር ነው። ከሰይጣን አገልጋዮች ጋር የሚያብር ሰው አዛዣቸውንም ጭምር መፍራት ያቆማል። ዳንኤል ሥራውን በትጋት በመሥራት ላይ ሳለ ለፍርድ በንጉሱ ፊት እንደቀረበው ሁሉ እኛም በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ ብንገኝ እግዚአብሔር እንደሚታደገን እርግጠኛ ልንሆን እንችላለን። ነገር ግን ራሳችንን ፈቅደንና ወደን ለፈተና አሳልፈን ከሰጠን አንድ ቀን መውደቃችን አይቀሬ ነው።ታተ 11.5

    ብዙውን ጊዜ ፈታኝ በይበልጥ በተሳካ መልኩ የሚሠራው በእርሱ ቁጥጥር ስር ይኖራሉ ተብለው በማይጠረጠሩ ግለሰቦች አማካኝነት ነው። ትምህርትና ልዩ ተስጥኦ ያላቸው በሰው ዘንድ አድናቆትና ክብር ያገኛሉ። ነገር ግን እነዚህ ችሎታዎች የፈሪሃ-እግዚአብሔርን ቦታ ሊተኩ ወይንም በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ ሊያስገኙ በፍጹም አይችሉም። የቀለም ትምህርት እውቀትና መክሊት ራሳቸው ከእግዚአብሔር የሚገኙ ስጦታዎች ናቸው። ነገር ግን እነዚህ ነገሮች በቅድስና ምትክ እንዲቆሙ ሲደረጉና ነፍስን ወደ እግዚአብሔር ከማቅረብ ይልቅ ከእርሱ ሲያርቁ፣ ያን ጊዜ መርገም እና ወጥመድ ይሆናሉ። ትህትና የተሞላበት የሚያምርና ጨዋ የሆነ ነገር ሁሉ የግድ ክርስቶሳዊ መሆን አለበት የሚል አመለካከት በብዙዎች ዘንድ ጎልቶ ይታያል። ይህ ትልቅ ስህተት ነው። በእርግጥ እነዚህ ነገሮች እውነተኛ ሃይማኖትን በተመለከተ ታላቅ አወንታዊ ተፅዕኖ ስለሚያሳድሩና መልካም ምስክርነት ስለሚሆኑ በእያንዳንዱ ክርስቲያን ባህሪ ውስጥ ሊንጸባረቁ ይገባል። ሆኖም ግን ለእግዚአብሔር ክብር መዋል አለባቸው። አለበለዚያ የጥፋት ኃይል ይሆናሉ። ጨዋና ምሁር፣ ለዛ ያለውና ስርዓት አክባሪ፣ በተለምዶ ግብረገባዊ ያልሆኑ ተብለው የሚታሰቡ ድርጊቶችን ለመፈጸም ጊዜ የሌለው ነገር ግን በሰይጣን እጅ የተሳለ መሣሪያ የሆነ ስንት አለ!። የዚህ አይነት ሰው መሰሪነቱ፣ ባህሪው የሚያሳድረው ተፅዕኖ እና ለሌሎች የሚያሳየው ምሳሌ፣ አላዋቂ ከሆኑት እና ካልተማሩት ይልቅ እጅግ አደገኛ የክርስቶስ ባላንጣ ያደርገዋል።ታተ 12.1

    በቅንነት በመጸለይ እና በእግዚአብሔር በመተማመን ሰለሞን ዓለምን ሁሉ ያስደነቀና ያስገረመ ጥበብ ባለቤት ሆነ። ነገር ግን ፊቱን ከኃይል ሰጭው በመመለሰ በራሱ መተማመን በጀመረ ጊዜ ለፈተና በቀላሉ ተዳረገ። ያም በሆነ ጊዜ፣ ለዚህ ከነገሥታት ሁሉ በጥበብ ለላቀው ንጉስ የተሰጡት እነዚያ ድንቅ ችሎታዎች ለነፍሳት ባላንጣ ውጤታማና ምቹ ወኪል አደረጉት።ታተ 12.2

    ሰይጣን ክርስቲያኖች እውነታውን እንዳያውቁ አእምሮአቸውን ለማጨለም ሳያቋርጥ በመስራት ላይ ሳለ ክርስቲያኖች ደግሞ መጋደላቸው፣ ከአለቆችና ከሥልጣናት ጋር ከዚህም ከጨለማ ዓለም ገዦች ጋር በሰማያዊም ስፍራ ካለ ከክፋት መንፈሳውያን ሠራዊት ጋር እንጂ ከደምና ከሥጋ ጋር እንዳይደለ በፍጹም መዘንጋት የለባቸውም። (ኤፌሶን 6፡12)። በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ጥንት የተሰጠው ያ ማስጠንቀቂያ በዘመናት መካከል ሰንጥቆ ዛሬም በእኛ ዘመን ጎልቶ ይሰማል፣ «በመጠን ኑሩ ንቁም፥ ባላጋራችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ ይዞራልና።» (1ኛ ጴጥሮስ 5፡8)። «የዲያብሎስን ሽንገላ ትቃወሙ ዘንድ እንዲቻላችሁ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ ልበሱ።» (ኤፌሶን 6፡11)።ታተ 12.3

    ከአዳም አንስቶ እስከ እኛ ዘመን ድረስ ታላቁ ጠላታችን የመጨቆን እና የማጥፋት ኃይሉን ሲጠቀም ቆይቷል። አሁን በቤተክርስቲያን ላይ ሊያደርግ ላለው ለመጨረሻ ዘመቻው በመዘጋጀት ላይ ይገኛል። ክርስቶስን ለመከተል የሚሹ ሁሉ ከዚህ ክፉ እና ቁጡ ጠላት ጋር መጋጨታቸው የግድ ነው። አንድ ክርስቲያን መለኮትን በመሰለ ቁጥር ለሰይጣን ጥቃት ምቹ ኢላማ ይሆናል። በእግዚአብሔር ሥራ ነቅተው የሚሰማሩና የጠላትን ማታለያዎች በማጋለጥ ስለክርስቶስ በሰዎች ፊት ለመመስከር የሚሹ በሙሉ ሐዋሪያው ጳውሎስ እንደተናገረው ጌታን በፍጹም ትህትና፣ በብዙ እንባ እና ፈተና እናገለግለዋለን በማለት ይመሰክራሉ።ታተ 12.4

    ሰይጣን ክርስቶስን ከባድ እና እጅግ ረቂቅ በሆነ ፈተና ሊያጠቃው ቢሞክርም በእያንዳንዱ ነጥብ ተረታ። እነዚያ ውጊያዎች ሁሉ የተካሄዱት በእኛ ምትክ ነበር። እነዚያ ድሎች ደግሞ እኛንም ድል እንድንቀዳጅ ያስችሉናል። ለሚፈልጉ ሁሉ ክርስቶስ ኃይልን ይሰጣል። ማንም ሰው ካለፈቃዱ በሰይጣን ሊሸነፍ አይችልም። ፈታኝ የማንንም ሰው ፈቃድ የመቆጣጠር ወይም ማንንም ኃጢአት እንዲሰራ የማስገደድ ኃይል የለውም። ነፍስን ሊያስጨንቅ ይችላል ነገር ግን መበከል አይችልም። ስቃይና ጣር ሊያመጣም ይችላል ነገር ግን ልብን ማርከስ አይችልም። ክርስቶስ ድል የማድረጉ እውነታ የእርሱን ተከታዮች ከኃጢአትና ከሰይጣን ጋር በሚያደርጉት ግብግብ በድፍረት ሊሞላቸው ይገባል።ታተ 12.5

    Larger font
    Smaller font
    Copy
    Print
    Contents