Go to full page →

5—የናቲቱ ኃላፊነት CLAmh 21

አብዛኛውን ጊዜ ልጆች የወላጆቻቸውን ምሳሌነት ይከተላሉ፡፡ የወላጆቹ ጤነኛነት ወይም በሽተኛነት፣ ጠባይ፣ አምሮትና የሞራል ልምድ ከሞላ ጎደል በልጆቻቸው ላይ ይታያል፡፡ የወላጆቹ ዓለማ፤ የአእምሮና የመንፈሳዊ ስጦታቸው ከፍ ያለ እንደመሆኑ መጠን የአካላቸው ኃይል በተሻለ አኳኋን ይዳብራል፤ ለልጆቻቸውም የተሻሉ የሕይወት መሣሪያዎች ሊያወርሷቸው ይችላሉ፡፡ ራሳቸውን በማሻሻል ወላጆች ኅብረተሰብንና የመጭውንም ትውልድ ሁናቴ ለመወሰን ይችላሉ፡፡ CLAmh 21.3

አባትና እናት የሆኑ ሁሉ ኃላፊነታቸው ምን እንደሆነ መረዳት አለባቸው፡፡ በዓለም ወጣቶችን የሚያደናቅፍ ሞልቷል፡፡ ብዙ ሰዎች ራስን በመውደድና በጊዜአዊ ደስታ በተሞላ ሕይወት ይታለላሉ፡፡ ወደ ደስታ ያደርሰናል ብለው በሚያስቡት መንገድ ላይ ምን ድብቅ አደጋ እንዳለ ወይም መንገዱ ራሱ የት እንደሚያደርስ አይገባቸውም፡፡ በአምሮትና በፍትወት ስግብግብነት ኃይላቸውን ስለሚያባክኑት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በዚህኛውም ሆነ በሚመጣው ዓለም ዋጋ የላቸውም፡፡ ወላጆች ልጆቻቸውን የዚህ ዓይነት ፈተና እንደሚያጋጥማቸው ማወቅ አለባቸው፡፡ አንድ ልጅ ከመወለዱ በፊት መጥፎውን ነገር ለማሸነፍ የሚያስችለው ዝግጅት ሊጀመርለት ይገባል፡፡ CLAmh 21.4

እናቲቱ የተለየ ኃላፊነት አለባት፡፡ ጽንሱ የሚያድገው ከእርስዋ ደም በመመገብ ስለሆነ አእምሮውንና ጠባዩን የሚያንጹ ነገሮች ታወርሰዋለች፡፡ ከሃይማኖተ ጽኑዋ “የንጉሡን ትእዛዝ ካልፈራችው” (ዕብራ 11፡23) ከዕብራዊት ዮኬብድ እሥራኤልን ያዳነው ሙሴ ተወለደ፡፡ የእስራኤልን የኃይማኖት ትምህርት ቤቶች ያቋቋመውን፤ ቅን ዳኛና የሥዕለት ልጅ የነበረውን ሳሙኤልን የወለደችው ሐና የጸሎትና የሃይማኖት ሴት ነበረች፡፡ ስለ ጌታችን አዋጅ ይናገር የነበረው ሰው (መጥምቁ ዮሐንስ) እናት የማርያም ዘመድ የነበረችው ኤልሳቤጥ ነበረች፡፡ CLAmh 22.1

እናቶች በኑሮ ልምዳቸው እንዴት ሊጠነቀቁ እንደሚገባ በመጽሐፍ ቅዱስ ተጠቅሷል፡፡ እግዚአብሔር ሳምሶንን የእሥራኤል መሪ አድርጎ ባስነሳበት ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ ለሴቲቱ ተገልጾ ለራስዋና ለልጁ እንዴት ልትጠነቀቅ እንደሚገባተት ነገራት፡፡ “ወይንና የሚያሰክር መጠጥ እንዳትጠጪ ንጹሕ ያልሆነም ነገር እንዳትበይ ተጠንቀቂ” አላት፡፡ መሳፍንት 13፡13 CLAmh 22.2

ብዙ ወላጆች በጽንሱ ላይ ሊደርስበት የሚችለውን እደቀላል ቢመለከቱትም እግዚአብሔር አቅልሎ አይመለከተውም፡፡ የእግዚአብሔር መልአክ ስለዚህ ጉዳይ ተልኮ ከመጣ፤ እንደዚሁም እግዚአብሔር ሁለት ጊዜ ምን ያህል መጠንቀቅ እንደሚገባ ከተናገረ እኛም ስለዚህ ነገር አጥብቀን ልናስብበት ይገባናል፡፡ CLAmh 22.3