ምዕራፍ 18—በቤት ውስጥ ደህንነት
ሰብአዊ ፍቅር ከመለኮታዊው ፍቅር ያገኘውን ነገር መጠቀም አለበት።--የጋብቻ ሕብረት ያለ ችግር ሊፈጠር የሚችለው በክርስቶስ ብቻ ነው። ሰብአዊ ፍቅር ከመለኮታዊ ፍቅር ጋር እጅግ የቀረበ ግንኙነት መፍጠር አለበት። [‹‹የሕይወት ብርታት ሰጭ ኃይል›› የሚለውን ክፍል 5ን ይመልከቱ።»] ጥልቅ የሆነ፣ እውነተኛና ራስ ወዳድነት የሌለበት ፍቅር ሊኖር የሚችለው ክርስቶስ በነገሰበት ቦታ ብቻ ነው። --MH 358 (1905). {1MCP 152.1}1MCPAmh 124.2
እግዚአብሔር እንዲሆን ከሚፈልገው ነገር ላይ መድረስ።--ወንዶችና ሴቶች እግዚአብሔር እንዲሆኑ ከሚፈልግባቸው ነገር መድረስ የሚችሉት ክርስቶስን እንደ ረዳታቸው ከተቀበሉት ነው። ሰብአዊ ጥበብ ሊያደርገው የማይችለውን ነገር ክርስቶስን በመውደድ ለእርሱ ራሳቸውን ለሚሰጡ የእርሱ ጸጋ ይፈጽምላቸዋል። የእርሱ ፈቃድ ልቦችን መነሻው ሰማያዊ በሆነ ግንኙነት ያስተሳስራል። ፍቅር ማለት ዝም ብሎ ለስለስ ያሉና ከሚገባው በላይ የመካካብ ቃላትን መለዋወጥ አይደለም። የሰማይ የሸማኔ ዕቃ ስስ የሆነ ድርና ማግን ይሸምናል፣ ነገር ግን በምድራዊ የሸማኔ ዕቃ ከሚሰራው ይልቅ የጠነከረ ነው። ውጤቱም በቀላሉ የሚቀደድ ጨርቅ ሳይሆን እርጅናን፣ ችግርንና ፈተናን መቋቋም የሚችል ጨርቅ ነው። ልብ ከልብ ጋር ዘላቂነት ባለው ወርቃማ የፍቅር ማሰሪያ ይተሳሰራል። --MH 362 (1905). {1MCP 152.2}1MCPAmh 124.3
ጋብቻን ስታሰላስሉ እያንዳንዱን አስተያየት መዝኑ።--ጋብቻን ለመፈጸም እያሰላሰሉ ያሉ ሰዎች የህይወት መዳረሻቸውን ለማጣመር እያሰቡ ያሉትን ሰው እያንዳንዱን አስተያየት መመዘንና የባሕርይ እድገትን ነቅተው መመልከት አለባቸው። ወደ ጋብቻ ሕብረት የሚመራ እያንዳንዱ እርምጃ እግዚአብሔርን ለማስደሰትና ለማስከበር እንዲቻል ትህትና፣ ራስን ዝቅ ማድረግ፣ ታማኝነትና ቅንነት ያለበት ዓላማ የሚታይበት ይሁን። ጋብቻ በዚህ ዓለምም ሆነ በሚመጣው ዓለም የወደፊት ሕይወትን ይነካል። እውነተኛ የሆነ ክርስቲያን እግዚአብሔር ማረጋገጫ የማይሰጠውን ምንም ዓይነት ዕቅድ አያቅድም። --MH 359 (1905). {1MCP 152.3}1MCPAmh 124.4
እውነተኛ የሆነ አንድነት የዓመታት ሥራ ነው።--ጋብቻ ምንም ያህል በጥንቃቄና በጥበብ ቢገባበትም የጋብቻ ሥነ ሥርዓት በተፈጸመ ጊዜ ሙሉ በሙሉ አንድ የሚሆኑ ጥንዶች በጣም ጥቂት ናቸው። በጋብቻ ቃል ኪዳን የተጣመሩ የሁለቱ ሰዎች እውነተኛ ውህደት ቀጥለው ባሉት ዓመታት ውስጥ የሚሰራ ሥራ ነው።--MH 359, 360 (1905). {1MCP 153.1}1MCPAmh 125.1
ዘለቄታ የሌለው የፍቅር ሀሳብ ይጠፋል።--ሕይወት የራሱን ግራ የሚያጋባና የሚያስጨንቅ ሸክም ይዞ አዲስ የተጋቡ ሙሽሮችን ሲጋፈጣቸው ብዙ ጊዜ በዓይነ ሕሊናቸው ስለ ጋብቻ ያስቡት የነበረው የፍቅር ስሜት ይጠፋባቸዋል። ባልና ሚስት አስቀድሞ በነበራቸው ግንኙነቶች ስለ እርስ በርስ ሊያውቁ ያልቻሉትን አሁን ያውቃሉ። ይህ በልምምዳቸው ውስጥ እጅግ ወሳኝ ወቅት ነው። የወደ ፊት ሕይወታቸው ደስታና ጠቃሚነት አሁን በሚወስዱት ትክክለኛ መንገድ ይወሰናል። ብዙ ጊዜ በእርስ በርሳቸው ላይ ያልተጠበቁ ጉድለቶችን ይመለከታሉ፣ ነገር ግን ፍቅር ያስተሳሰራቸው ልቦች ከዚህ በፊት ያልታወቁ ጥሩ ነገሮችንም ይመለከታሉ። ሁሉም ጉድለቶችን ሳይሆን ጥሩ ነገሮችን ለማግኘት ይፈልጉ። ብዙ ጊዜ በሌላ ሰው ላይ የሚታየንን ነገር የሚወስነው የራሳችን አመለካከትና ከቦን ያለው ከባቢ አየር ነው። {1MCP 153.2}1MCPAmh 125.2
ፍቅርን መግለጽን እንደ ድክመት ስለሚቆጥሩ ሌሎች እንዳይቀርቡአቸው ራሳቸውን የሚያቅቡ ብዙ ሰዎች አሉ። ይህ መንፈስ የርኅራኄ ማዕበልን ይገታል። ማህበራዊና የልግስና ስሜቶች ሲታመቁ ይጠወልጉና ልብ ባዶና ቀዝቃዛ ይሆናል። ከዚህ ስህተት ልንጠነቀቅ ይገባል። ፍቅር ካልተገለጸ ዕድሜ አይኖረውም። ከአንተ ጋር ግንኙነት ያለው ሰው ደግነትንና ርኅራኄን በማጣት መራብ የለበትም። --MH 360 (1905). 154 {1MCP 153.3}1MCPAmh 125.3
ፍቅር የከበሩ ዓላማዎችን ለመፈጸም ያነሳሳል።--እያንዳንዱ ሰው ፍቅርን ከመጠየቅ ይልቅ ይስጥ። በውስጣችሁ የከበረውን ነገር አሳድጉት፣ በእርስ በርሳችሁ ውስጥ ጥሩ ነገሮችን ለማግኘት ፈጣኖች ሁኑ። ሰው እንደሚያደንቀን ማወቅ አስደናቂ የሆነ ማነሳሻና እርካታ ነው። ርኅራኄና አክብሮት ለጥሩ ነገር የሚደረገውን ጥረት ስለሚያደፋፍር ፍቅር የከበሩ ዓላማዎችን እየቀሰቀሰ ሳለ ራሱም እየጨመረ ይሄዳል። --MH 361 (1905). {1MCP 154.1}1MCPAmh 125.4
ግለሰባዊነት መጨፍለቅ የለበትም።--ባልም ሆነ ሚስት የራሱን ወይም የራሷን ግለሰባዊነት በሌላው መቀላቀል የለበትም/ የለባትም። እያንዳንዳቸው ከእግዚአብሔር ጋር የግል ግንኙነት አላቸው። እያንዳንዳቸው ከእርሱ ‹‹ትክክል የሆነው ነገር ምንድን ነው?›› ‹‹ስህተት የሆነውስ ምንድን ነው?›› ‹‹የሕይወትን ዓላማ በተሻለ ሁኔታ መፈጸም የምችለው እንዴት ነው?›› ብለው ይጠይቁ። የፍቅራችሁ ሙላት ሕይወቱን ለእናንተ ወደ ሰጠው ወደ እርሱ ይፍሰስ። በሁሉም ነገር ክርስቶስን መጀመሪያ፣ መጨረሻና ከሁሉም የተሻለ አድርጉት። ለእርሱ ያላችሁ ፍቅር ጥልቅና ጠንካራ ሲሆን ለእርስ በርሳችሁ ያላችሁ ፍቅርም እየነጻና እየጠነከረ ይሄዳል።--MH 361 (1905). {1MCP 154.2}1MCPAmh 126.1
የራሳችን ግለሰብነት ስላለን የሚስት ግለሰብነት በባሏ ግለሰብነት ውስጥ በፍጹም መስመጥ የለበትም። እግዚአብሔር ፈጣሪያችን ነው። እኛ በድነትም በመቤዠትም የእርሱ ነን። እግዚአብሔር የሞራል ኃይል ስለሚሰጠን፣ ብቃትን ስለሚሰጠን፣ ማስተዋልን ስለሚሰጠን፣ ለእርሱ ምን ያህል መልሰን እንደምንሰጥ ማየት እንፈልጋለን፤ እነዚህን የከበሩ ስጦታዎች ለስሙ ክብር እንድንጠቀም ይፈልግብናል። --MS 12, 1895. {1MCP 154.3}1MCPAmh 126.2
ሙሉ በሙሉ ራስን ማስገዛት ለኢየሱስ ብቻ።--ሚስት ሁል ጊዜ እግዚአብሔርን እንድትፈራና የእርሱን ክብር በፊቷ እንድትጠብቅ እግዚአብሔር ይፈልግባታል። ሙሉ በሙሉ መገዛት የሚያስፈልገው በራሱ ዘላለማዊ በሆነ ዋጋ የራሱ ልጅ አድርጎ ለገዛት ለጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው።…እርሷን ክርስቶስ ስለገዛት ግለሰብነቷ ከባለቤቷ ግለሰብነት ሊደባለቅ አይችልም።--Lt 18b, 1891. (AH 116.) {1MCP 154.4}1MCPAmh 126.3
የተፈጠረው አንድነት ስህተት ነው የሚል አስተሳሰብ መስተናገድ የለበትም።--ምንም እንኳን ችግሮች፣ ግራ መጋባቶች እና ተስፋ መቁረጦች ሊነሱ ቢችሉም ባልም ሆነ ሚስት ጥምረታቸው ስህተት ወይም ተስፋ አስቆራጭ መሆኑን የሚገልጸውን ሀሳብ አያስተናግዱ። ለእርስ በርሳችሁ መሆን የምትችሉትን ሁሉ ለመሆን ወስኑ። ጅምር ላይ የነበረውን ትኩረት መስጠት ቀጥሉበት። የሕይወትን ጦርነቶች ስትዋጉ በእያንዳንዱ መንገድ እርስ በርሳችሁ ተበረታቱ። የእርስ በርሳችሁን ደስታ ለመጨመር ጥናት አድርጉ። የጋራ ፍቅርና የጋራ መቻቻል ይኑር። ጋብቻ የፍቅር መጨረሻ ከመሆን ይልቅ የፍቅር ጅምር ይሆናል። የእውነተኛ ጓደኝነት ግለት፣ ልብን ከልብ ጋር የሚያስተሳስር ፍቅር፣ የሰማይ ደስታ ቅምሻ ነው።--MH 360 (1905). {1MCP 154.5}1MCPAmh 126.4
በማሰብ ችሎታ ቁጥጥር ሥር ያለ ግንኙነት።--የጋብቻ ግንኙነትን እግዚአብሔር ከቀደሳቸው ሥርዓቶች ውስጥ እንደ አንዱ አድርገው የሚመለከቱ ሰዎች፣ በእርሱ ቅዱስ ቃል ተጠብቀው፣ በአእምሮ የማሰብ ኃይል ቁጥጥር ሥር ይሆናሉ። የጋብቻ ግንኙነት የሚሰጣቸውን እያንዳንዱን ጥቅም ውጤት በጥንቃቄ ይመለከታሉ። እንደዚህ ያሉ ሰዎች ልጆቻቸው እንዲንከባከቡአቸው፣ ድምቀታቸው መታየት እንዲችል ሥነ-ሥርዓትን በማስተማር ከተፈጥሮአቸው ሸካራ ክፍሎችን እንዲያስወግዱ ከእግዚአብሔር የተሰጡአቸው የከበሩ እንቁዎች እንደሆኑ ይሰማቸዋል። በሕይወታቸው መልካም እንዲያደርጉ፣ በብርሃናቸው ሌሎችን እንዲባርኩ፣ ዓለም እነርሱ ስለሚኖሩበት የተሻለ ቦታ እንዲሆን፣ እና በመጨረሻም ከፍ ላለ ሕይወት፣ ለተሻለው ዓለም ገጣሚዎች እንዲሆኑ፣ በእግዚአብሔርና በበጉ ፊት ለዘላለም እንዲያበሩ፣ ባሕርዮቻቸውን ለመመስረት እጅግ የከበረ ግዴታ እንዳለባቸው ይሰማቸዋል።--HL (Part 2) 48, 1865. {1MCP 155.1}1MCPAmh 126.5
በደንብ የተደራጀ ቤተሰብ።--የቤተሰብ ድርጅት በደንብ የተቀናጀ መሆን አለበት። አባትና እናት በአንድነት ኃላፊነቶቻቸውን መመልከት አለባቸው። ለልጆቻቸው እጅግ ከፍ ያለ መልካም ነገር እንዲገጥማቸው በአንድነት መስራት አለባቸው። በመካከላቸው ልዩነት መኖር የለበትም። በልጆቻቸው ፊት በፍጹም አንዳቸው የሌላኛውን እቅድ መተቸት ወይም በእርስ በርሳቸው ውሳኔ (ፍርድ አሰጣጥ) ላይ ጥያቄ ማንሳት የለባቸውም። ሚስት ልምድ የሌላት ከሆነች፣ ባል ለልጆቹ ድነት በሚሰራበት ጊዜ የእሷ ሥራ የባለቤቷን ሥራ የበለጠ ከባድ እንዲሆን የሚያደርግበትን ቦታ ለማግኘት መጣር አለባት።ባልም ለሚስቱ ጥበብ ያለበትን ምክርና ፍቅር ያለበትን ማበረታቻ በመስጠት እጆቿን መያዝ አለበት።--RH, July 8, 1902. {1MCP 155.2}1MCPAmh 127.1
ወላጆች ራሳቸውን መግዛት አለባቸው።--ቤተሰቦቻቸውን በተሳካ ሁኔታ የሚያስተዳድሩ ሰዎች መጀመሪያ ራሳቸውን መግዛት አለባቸው። በቤተሰቦቻቸው ውስጥ መልካም ቃላት ብቻ እንዲነገሩ ከፈለጉ፣ ልጆቻቸው ከከናፍራቸው መልካም ቃላትን ብቻ እንዲሰሙ ያድርጉ። ዘር ሲዘራ ያንኑ የሚመስል መከር ይሰጣል። ወላጆች በቃልና በሕይወት ምሳሌነት በማስተማር መስራት ያለባቸው የከበረና ቅዱስ ሥራ አለ። ልጆቻቸውን ገና በልጅነት ዕድሜያቸው፣ የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታይ በመሆን መገንዘብ ያለባቸውን ብልህነት ያለበትን እውቀት እንዲቀበሉ ገጣሚዎች በማድረግ፣ ለእግዚአብሔር የማቅረብ ግዴታ አለባቸው። የመጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያኖች እንደሆኑ የሚናገሩ ሰዎች እግዚአብሔርን የማይፈሩና የማይወዱ ልጆች ካሉአቸው ምክንያቱ ወላጆች እያሳዩ ያሉት ምሳሌ ትክክለኛ ስላልሆነ ነው። የውሸትና የማጭበርበር ዘሮች ስለተዘሩ የእሾክና የአሜካላ ምርት ሰጥተዋል። --MS 59, 1900. {1MCP 156.1}1MCPAmh 127.2
ደግ ቃላትና ፈገግታ ለቤተሰብ።--ደግነትን ማሳደግ፣ በልባችን የክርስቶስን ፍቅር ማግኘት እና እንደ ሰላም ፈጣሪዎችና የክርስቶስ ተከታዮች ለዘላለም ሕይወት የሚሆንን መልካም ዘር መዝራት መልካም ዕድል ብቻ ሳይሆን ግዴታችንም ነው። የክርስቶስ ተከታይ ነን ባዮች ብዙ መልካምና ጠቃሚ ችሎታዎች ሊኖሩአቸው ይችላሉ፤ ነገር ግን ባሕርዮቻቸው ደግነት በሌለበት፣ ደስታ በጎደለበት፣ ስህተት ፈላጊ በሆነ፣ በጭካኔ በሚፈርድ የቁጣ ስሜት ተበላሽተዋል። ጥርጣሬንና አለመተማመንን የሚያሳይ ባል ወይም ሚስት በቤት ውስጥ ጠብንና መለያየትን ይፈጥራል/ትፈጥራለች። ማናቸውም ቢሆኑ የደግነት ቃላቶቻቸውንና ፈገግታቸውን ለእንግዶች ብቻ በማስቀመጥ በቤት ውስጥ ብስጭትን እያሳዩ ሰላምንና እርካታን ማባረር የለባቸውም።--Lt 34, 1894. (HC 179.) {1MCP 156.2}1MCPAmh 127.3
ስድ/ያልታረመ ንግግርን መራቅ።--አባቶችና እናቶች፣ ባሎችና ሚስቶች ሆይ፣ የወረደ አስተሳሰብንና ስድ ንግግርን እንዳትለማመዱ እማጸናችኋለሁ። ሸካራ አባባሎች፣ የወረዱ ቀልዶች፣ በቤት ሕይወት ትህትና ማጣት በእናንተ ላይ አሻራ ስለሚተው ተደጋግሞ የሚፈጸም ከሆነ ሁለተኛ ባሕርይ ይሆናል። ቤት በስድ ንግግር፣ በፍትወትና በውንጀላ መርከስ (መበከል) የሌለበት እጅግ ቅዱስ ቦታ ነው። ‹‹ሥራህን አውቃለሁ›› የሚል ምስክር አለ። ፍቅር፣ እውነት፣ ደግነትና መቻቻል በልብ የአትክልት ቦታ ውስጥ የሚያድጉ ተክሎች ይሁኑ።--Lt 18b, 1891. {1MCP 156.3}1MCPAmh 128.1
ባለጌነትን ወይም ትህትና የሌለበትን ባሕርይ በፍጹም አታሳዩ።--በቤተ ሰብ ክበብ ውስጥ ባለጌነትን፣ ደግነት የጎደለውንና ትህትና የሌለውን ባሕርይ በፍጹም አታሳዩምን? በቤታችሁ ውስጥ ደግነት የሚጎድላችሁ ከሆነ፣ የትምህርት እውቀታችሁ የፈለገውን ያህል ከፍ ያለ ቢሆን፣ የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት እየተላለፋችሁ ነው። --RH, Mar 29, 1892. {1MCP 157.1}1MCPAmh 128.2
በቤት ሕይወት ጓደኞች ጣልቃ መግባት የለባቸውም (ለአንድ ወጣት የተሰጠ ምክር)፡--የቤተሰብ ክበብ እንደ ቅዱስ ቦታ፣ እንደ ሰማይ ምሳሌ፣ ራሳችንን የምናንጸባርቅበት መስተዋት እንደሆነ ተደርጎ መታየት አለበት። ጓደኞችና በቅርበት የምንተዋወቃቸው ሰዎች ሊኖሩን ይችላሉ፣ ነገር ግን በቤተሰብ ሕይወት ውስጥ ጣልቃ መግባት የለባቸውም። ምቾት፣ እረፍትና የመታመን ስሜት የሚሰጥ ጠንካራ የባለቤትነት ስሜት መሰማት አለበት። {1MCP 157.2}1MCPAmh 128.3
ነገር ግን ከሌሎች ሴቶችና ልጃገረዶች ጋር ያለህ ግንኙነት ለእነርሱ የፈተና ምንጭ ስለሆነ የጋብቻ ግንኙነት በእያንዳንዱ ወንድና ሴት ላይ የሚያስቀምጠውን ገደብ አልፈው ለመሄድ ነጻነት እንዳላቸው ወደመቁጠር መርቶአቸዋል። አንተ ባትገነዘበውም ለደስታ ያለህ ፍቅርና ያደፋፈርከው መንፈስ ሌሎች የጋብቻ ግንኙነትን ቅድስና እንዲገነዘቡ አላደረገም። {1MCP 157.3}1MCPAmh 128.4
ተግባራዊ የሆነ የቤት ሕይወት ትልቁ የባሕርይ መፈተኛ ነው። ሰው ባሕርዩን የሚወስነው በቤት ውስጥ በሚያሳየው ገር አሳቢነት፣ ትዕግስትን፣ ደግነትንና ፍቅርን በመለማመድ ነው። --Lt 17, 1895. {1MCP 157.4}1MCPAmh 129.1
ሚስቶች የፍቅር ቃላትን ይናፍቃሉ።--ብዙ ሴቶች እንደ ሕይወት ጓደኞቻቸው አድርገው ከመረጡአቸው ባሎቻቸው የፍቅርና የደግነት ቃላትን እና የሚገባቸውን ትኩረትና ትህትና ለማግኘት ይናፍቃሉ። ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ፍቅርን በሕይወት ያቆዩትን እና የመረጡአቸውን ጓደኞች ለማግኘት አስፈላጊ እንደሆኑ ተሰምቶአቸው የነበሩትን አክብሮትን፣ ትኩረት መስጠትን፣ መልካም የአድናቆት ቃላትን መናገርንና የሕይወት ትህትናን በማሳደግ ቀጥለውበት ቢሆን ኖሮ ምን ያህል ችግርና የዋይታና የሀዘን ማዕበሎች መቅረት በቻሉ ነበር። {1MCP 157.5}1MCPAmh 129.2
ባልና ሚስት እነዚህን ፍቅርን የሚመግቡ ትኩረቶች ማሳደጋቸውን ቀጥለው ቢሆን ኖሮ ከእርስ በርሳቸው ጋር በሚፈጥሩት ሕብረት ደስተኛ ይሆኑ ነበር፣ በቤተ ሰቦቻቸው ላይም የሚቀድስ ተጽእኖ ይኖራቸው ነበር። በራሳቸው ትንሽ የደስታ ዓለም ስለሚኖራቸው ከዚህ ዓለም ውጭ ወዳሉ አዳዲስ ትኩረትን ወደሚስቡ ነገሮችና የፍቅር ደንበኞች ለመሄድ አይመኙም ነበር። ብዙ ሚስቶች ደግነት ባለበት ትኩረትና በቃላት የሚገለጹ፣ ርኅራኄና ፍቅር ያለባቸውን የማደፋፈሪያ ቃላት ከማጣታቸው የተነሣ ታመው ያለ ዕድሜያቸው ሞተዋል። --Lt 27, 1872. {1MCP 158.1}1MCPAmh 129.3
ባል የበሽታ በርን መዝጋት ይችላል።-- ባል በቤተሰቡ ላይ ትልቅ ፍላጎት ማሳየት አለበት። በተላይ ደካማ ለሆነችው ሚስቱ ስሜቶች የሚጠነቀቅ እጅግ ደግ መሆን አለበት። የብዙ በሽታዎችን በር መዝጋት ይችላል። ደግ፣ አስደሳችና የሚያበረታቱ ቃላት እጅግ ፋዋሽ ከሆኑ መድኃኒቶች ይልቅ ውጤታማ ናቸው። እነዚህ ነገሮች ላዘነና ተስፋ ለቆረጠ ሰው ልብ ድፍረትን ያመጣሉ፣ በደግነት ተግባራትና በሚያበረታቱ ቃላት አማካይነት በቤተሰብ ውስጥ የሚመጣው ደስታና የፀሐይ ብርሃን ጥረቱን አስር እጥፍ ትርፋማ አድርጎ ይመልሳል። {1MCP 158.2}1MCPAmh 129.4
ባል ልጆቹን የማሰልጠን አብዛኛው ጫና በእናት ላይ እንደሚያርፍና አእምሮአቸውን በመቅረጽ ረገድ ብዙ የምታደርገው ነገር እንዳለ መገንዘብ አለበት። ይህ እጅግ ደግ የሆኑ ስሜቶቹን ሥራ ላይ እንዲያውልና በጥንቃቄ ሸክሞቿን እንዲያቀልላት ጥሪ ማድረግ አለበት። በትልቅ ፍቅሩ ላይ እንድትደገፍ ማደፋፈር እና ብርታት፣ ሰላምና ለደከሙት የመጨረሻ እረፍት ወዳለበት ወደ ሰማይ አእምሮዋን መምራት አለበት። {1MCP 158.3}1MCPAmh 129.5
ፊቱን አጨልሞ ወደ ቤቱ መምጣት የለበትም፣ ነገር ግን በመገኘቱ በቤተሰቡ ውስጥ የፀሐይ ብርሃንን ማምጣትና ሚስቱ ወደ ላይ እንድትመለከትና በእግዚአብሔር እንድታምን ማደፋፈር አለበት። በአንድነት የእግዚአብሔር ተስፋዎች እንዲሰጡአቸው መጠየቅና የእርሱን የበረከት ብልጽግና በቤተሰብ ውስጥ ማምጣት ይችላሉ። ደግ አለመሆን፣ ብሶት ማውራት፣ እና ቁጣ በመኖሪያችን ኢየሱስ እንዳይገኝ ይዘጋሉ። የማያስደስቱ ቃላት፣ ደስተኛ አለመሆንና ጠብ ካለበት ቤት የእግዚአብሔር መላእክት እንደሚሸሹ አየሁ።--1T 306, 307 (1862). {1MCP 158.4}1MCPAmh 130.1
ባል የቤተሰቡ ራስ።-- ባልና አባት የቤተሰቡ ራስ ነው። ሚስት ፍቅርና ርኅራኄን እንዲሰጣትና ልጆችን ስታሰለጥን እንዲረዳት ወደ እርሱ ትመለከታለች፤ ይህ ትክክል ነው። ልጆች የእርሱም የእርሷም ስለሆኑ እርሱም በእነርሱ ደህንነት ፍላጎት አለው። ልጆች ወደ አባታቸው የሚመለከቱት ድጋፍና ምሪት እንዲሰጣቸው ነው፤ ስለ ሕይወትና የእርሱን ቤተሰብ መክበብ ስለለባቸው ግንኙነቶች ትክክለኛ የሆነ አመለካከት ሊኖረው ይገባል፤ የልጆቹን እግር በትክክለኛ መንገድ ላይ ለመምራት ከሁሉም በላይ በእግዚአብሔር ፍቅርና ፍርሃት፣ እንዲሁም በቃሉ ትምህርት ቁጥጥር ሥር መሆን አለበት። .--MH 390 (1905). {1MCP 159.1}1MCPAmh 130.2
ሚስት ለባሏ ‹‹ረዳት›› ነች።--ለአዳም ጓደኛ የሰጠው እግዚአብሔር ራሱ ነበር። እርሱ ‹‹ረዳት›› ሰጠው››-የምትስማማውን ረዳት-ጓደኛው ለመሆን ገጣሚ የነበረችውንና በፍቅርና በርኅራኄ አብራው የምትሆነውን ረዳት ሰጠው። ሄዋን የተፈጠረችው ከአዳም ጎን ከተወሰደው የጎድን አጥንት ነበር፣ ይህ የሚያሳየው እንደ ራስ ሆና ልትቆጣጠረውም ሆነ የበታች ሆና ከእግሩ በታች እንድትረገጥ ሳይሆን፣ ነገር ግን እኩል ሆና ከጎኑ እንድትቆም፣ እንዲወዳትና እንዲከላከልላት ነበር። የወንድ አካል፣ አጥንት ከአጥንቱና ሥጋ ከሥጋው ስለነበረች ሁለተኛ ራሱ ነበረች፤ ይህ የሚያሳየው በዚህ ግንኙነት ውስጥ ሊኖር የሚገባው የቀረበ አንድነትና የፍቅር ግንኙነት ነው። --PP 46 (1890). {1MCP 159.2}1MCPAmh 130.3
በቤት ክበብ ውስጥ እንዴት ሰላም መፍጠር እንደሚቻል።--ባል እያንዳንዱ እውነተኛ ክርስቲያን ሊኖረው የሚገባ የባሕርይ ታላቅነት፣ የልብ ንጽህና፣ የአእምሮ ከፍታ ሲኖረው በጋብቻ ግንኙነት ውስጥ ይገለጣል።--ሚስቱን በጤንነትና በድፍረት ይጠብቃታል። የማጽናኛ ቃላት ለመናገር፣ በቤት ክበብ ውስጥ የሰላም ከባቢ አየር ለመፍጠር ጥረት ያደርጋል። --MS 17, 1891. (AH 228.) {1MCP 159.3}1MCPAmh 130.4
ባሎች በኤፌሶን መጽሐፍ ውስጥ የተሰጠውን ምሳሌ፣ ክርስቶስ ከቤተ ክርስቲያን ጋር ያለውን ግንኙነት፣ ማጥናትና ምን ማለት እንደሆነ ለማወቅ መሻት አለባቸው። ባል በቤተ ሰቡ ውስጥ አዳኝ መሆን አለበት። እግዚአብሔር በሰጠው የከበራ ወንድነት ሚስቱንና ልጆቹን ከፍ ለማድረግ ሁል ጊዜ እየፈለገ ይቆማልን? በአከባቢው ንጹህና ጣፋጭ አየር ይተነፍሳልን? ሥልጣን እንዳለው ተሰምቶት የክርስቶስን ፍቅር በቤት ውስጥ የሚኖር መርህ በማድረግ ይህን ፍቅር በትጋት ያሳድገዋልን? MS 17, 1891. (AH 117.) {1MCP 160.1}1MCPAmh 131.1
ባል በሥልጣኑ ላይ ትኩረት ማድረግ የለበትም።--ባል ሁል ጊዜ የቤተ ሰብ ራስ በሆነበት ስልጣን ላይ ትኩረት ማድረግ የወንድነት ማረጋገጫ አይደለም። ሥልጣን እንዳለው ለማሳየት ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ጥቅሶችን መጥቀስ ለእርሱ ያለውን አክብሮት አይጨምርም። ሚስቱ፣ የልጆቹ እናት፣ የእርሱን ዕቅዶች ስህተት እንደሌለባቸው አድርጋ እንድትተገብር መጠየቅ ወንድነቱን አይጨምርም። {1MCP 160.2}1MCPAmh 131.2
ጌታ ባልን የሚስት ራስ አድርጎ ያስቀመጠው እንዲከላከልላት ነው፤ ክርስቶስ የቤተ ክርስቲያን ራስና የምስጢራዊው አካል አዳኝ እንደሆነ ሁሉ ባልም የቤተሰብ አባላትን አንድ ላይ የሚያስተሳስር ማያያዣ ገመድ ነው። እያንዳንዱ እግዚአብሔርን እወዳለሁ የሚል ባል ስልጣኑን በተመለከተ እግዚአብሔር የሚፈልግበትን ነገሮች በጥንቃቄ ያጥና። ክርስቶስ ሥልጣኑን የተጠቀመው በጥበብ፣ በደግነትና በጨዋነት ነበር፤ ስለዚህ ባልም ሥልጣኑን ሲጠቀም ታላቁን የቤተ ክርስቲያን ራስ ምሳሌ ይከተል። --Lt 18b, 1891. (AH 215.) {1MCP 160.3}1MCPAmh 131.3
ባል ማዕረጉን ይዞ እንዲቆይ ሚስት በደስታ መደገፍ አለባት።--በሚስት በኩልም ብዙ ጊዜ ስህተት እንዳለ እንዳይ ተደርጌያለሁ። የራሷን መንፈስ ለመቆጣጠርና ቤትን ደስተኛ ለማድረግ ጠንካራ ጥረት አታደርግም። በእርሷ በኩል ብዙ ጊዜ አለመደሰትና ብሶት መናገር አለ። ባል ከሥራው ደክሞትና ግራ ተጋብቶ ሲመጣ የሚያስደስቱና የሚያበረታቱ ቃላት በመስማት ፈንታ ደመና የሸፈነውን ግንባር ይጋፈጣል። እርሱም ሰብአዊ ፍጡር ስለሆነ ለሚስቱ ያለው ፍቅር ይጠፋል፣ ለቤቱ ያለውን ፍቅርም ያጣል፣ መንገዱ ይጨልምበታል፣ ድፍረቱም ይጠፋል። ከዚህ የተነሣ ለራሱ ያለውን ክብርና እግዚአብሔር እንዲጠብቀው የሚፈልግበትን ማዕረግ ይተዋል። {1MCP 160.4}1MCPAmh 131.4
ክርስቶስ የቤተ ክርስቲያን ራስ እንደሆነ ሁሉ ባልም የቤተ ሰብ ራስ ነው፤ የእርሱን ተጽእኖ ዝቅ ለማድረግና ከዚያ ከከበረውና ኃላፊነት ካለበት ቦታ ለማውረድ ሚስት የምትከተለው ማንኛውም መንገድ እግዚአብሔርን አያስደስተውም። ፍላጎቶቿንና ፈቃድዋን ለባልዋ ማስገዛት የሚስት ተግባር ነው። ሁለቱም መሸናነፍ አለባቸው፣ ነገር ግን የእግዚአብሔር ቃል የባል ውሳኔ መከበር እንዳለበት ይናገራል። ሚስት መካሪዋና ጠባቂዋ እንዲሆን ለመረጠችው ሰው መገዛት ክብሯን አይቀንስም። ባል በቤቱ ውስጥ ያለውን ሥልጣን ቅንነትን ሁሉ እያሳየ ግን ውሳኔን በመስጠት ማቆየት አለበት።--1T 307, 308 (1862). {1MCP 161.1}1MCPAmh 132.1
ሰው ማህበራዊ ፍጡር ነው።--እግዚአብሔር በምድር ላይ ከፈጠራቸው ፍጡራን መካከል ከሰው ጋር እኩል የሚሆን አንድም ፍጡር አልነበረም። ‹‹እግዚአብሔር አምላክም አለ፤ ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም፤ የምትመቸውን ረዳት እፈጥርለታለሁ›› (ዘፍ. 2፡ 18)። ሰው ብቻውን እንዲኖር አልተፈጠረም፤ ማህበራዊ ፍጡር እንዲሆን ነበር የተፈጠረው። ያለ ጓደኛ ውብ የነበሩ የኤደን ቦታዎችና አስደሳች ሥራዎች ፍጹም የሆነ ደስታን መስጠት አይችሉም ነበር። ከመላእክት ጋር የሚያደርጋቸው ግንኙነቶች እንኳን ለርኅራኄና ለጓደኝነት የነበረውን ፍላጎት ሊያረኩ አይችሉም ነበር። ለመውደድና ለመወደድ ተመሳሳይ የሆነ ተፈጥሮ ያለው ማንም አልነበረም። --PP 46 (1890). {1MCP 161.2}1MCPAmh 132.2
በቤት ውስጥ መጣጣም ሊኖር የሚችለው በእግዚአብሔር መንፈስ ብቻ ነው።--የእግዚአብሔር መንፈስ ሊኖረን ይገባል፣ ካልሆነ ግን በቤት ውስጥ መጣጣም በፍጹም ሊኖረን አይችልም። ሚስት፣ የክርስቶስ መንፈስ ካላት፣ ለቃላቶቿ ትጠነቀቃለች፤ መንፈሷን ትቆጣጠራለች፣ ትገዛለች፣ ነገር ግን ባሪያ እንደሆነች ሳይሆን የባሏ ጓደኛ እንደሆነች ይሰማታል። ባል የእግዚአብሔር አገልጋይ ከሆነ፣ በሚስቱ ላይ ጌታ አይሆንም፤ ጭፍንና የፈለገውን በኃይል በማስፈራራት የሚያገኝ አይሆንም፣ የቤት ፍቅርን ከመጠን በላይ በመጠንቀቅ መንከባከብ አንችልም። ቤት፣ የእግዚአብሔር መንፈስ የሚኖርበት ከሆነ የሰማይ ምሳሌ ነው። --Lt 18-b 1891. (AH 118.) 162 {1MCP 161.3}1MCPAmh 132.3
የውስጥ ክበብ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው።--ኃይሎቻችን ሁሉ በክርስቶስ አገልግሎት ላይ መዋል አለባቸው። ይህ ሁላችንም ለእግዚአብሔር ያለብን ዕዳችን ነው። የታደሰው ሰው፣ ከክርስቶስ ጋር ግንኙነት በመፍጠር፣ ከእግዚአብሔር ጋር ወደ ነበረው ግንኙነት ተመልሶ እየመጣ ነው። የክርስቶስ ተወካይ ስለሆነ ሁል ጊዜ መጸለይና ለጸሎት መንቃት አለበት። ሥራዎቹ በቅርብና በሩቅ ይጠብቁታል። የመጀመሪያ ሥራው ለልጆቹና ለቅርብ ዘመዶቹ ነው። ውጭ ላለው ሰፊ ክበብ ለመሥራት ብሎ የውስጥ ክበብን ችላ ለማለት ምንም ነገር ምክንያት ሊሆንለት አይችልም። {1MCP 162.1}1MCPAmh 132.4
በመጨረሻው መልስ በሚሰጥበት ቀን አባቶችና እናቶች ስለ ልጆቻቸው መልስ እንዲሰጡ ይጠየቃሉ። ወላጆች ወደዚህ ዓለም የማምጣት ኃላፊነት ወስደው ላመጡአቸው ነፍሳት ድነት ምን እንዳደረጉና እንደተናገሩ ይጠየቃሉ። ጠቦቶቻቸውን እንግዶች እንዲጠብቁአቸው በመተው ችላ ብለዋቸዋልን? አባቶችና እናቶች ሆይ፣ ልጆቻችሁ በእርኩሰትና በኃጢአት እንዲያድጉ እየፈቀዳችሁ ነው ወይ? ለሌሎች ያደረጋችሁት ብዙ መልካም ነገር ስለ ልጆቻችሁ በእግዚአብሔር ዘንድ ያለባችሁን ዕዳ አይሰርዝም። መቅደም ያለበት የቤተሰባችሁ መንፈሳዊ ጦርነት ነው። ለእግዚአብሔር መልስ እንደሚሰጡ ሰዎች ሆናችሁ ስለ እነርሱ በመስራት ወደ ቀራኒዮ መስቀል ውሰዱአቸው። --MS 56, 1899. {1MCP 162.2}1MCPAmh 133.1