Loading...
Larger font
Smaller font
Copy
Print
Contents
የአድቬንቲስት ቤት - Contents
 • Results
 • Related
 • Featured
No results found for: "".
 • Weighted Relevancy
 • Content Sequence
 • Relevancy
 • Earliest First
 • Latest First

  ምዕራፍ ስድሳ ሁለት—ቁጠባ ሊተገበር ይገባዋል

  “ትርፍራፊውን ሰብስቡ” ፦ ስለ ገንዘብ አያያዝ ሊተኮርበት የሚገባውን ትምህርት በአንድ ወቅት ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጣቸው። ትምህርቱን ሲያዳምጡት የነበሩትን ሰዎች በታምሩ መገባቸው፤ ሆኖም ሁሉም ከጠገቡና ከረኩ በኋላ ትራፊው እንዲባክን አልፈቀደም። በአስፈለጋቸው ጊዜ በመለኮታዊ ኃይሉ ብዙ ሕዝብን የመገበ እርሱ ከትርፍራፊው አንድም እንዳይወድቅ ይሰበስቡት ዘንድ ደቀ መዛሙርቱን አዘዛቸው። ይህ ትምህርት የተሰጠው በክርስቶስ ዘመን ለነበሩት እንደሆነ ሁሉ ዛሬም ለእኛ ትምህርት ነው። የእግዚአብሔር ልጅ ጊዜያዊ ለሆነው ሕይወት የሚስፈልጉ ነገሮች ይቀርቡ ዘንድ ግድ ይለዋል። እንደዚህ ዓይነቱን ግብዣ ባሻው ጊዜ ማድረግ ቢችልም ቅሉ ከመብል በኋላ የተቆራረሱትን ፍርፋሪዎች ቸል አላላቸውም። 1Testimonies for the Church, Vol. 4, pp. 572, 573.AHAmh 277.1

  የየሱስ ክርስቶስ አስተምህሮቶች በእያንዳንዱ የሕይወት ምዕራፍ ሊተገበሩ ይገባቸዋል። ቆጣቢነት በሁሉም ነገሮች ላይ ሊተገበር ይገባዋል። ምንም እንዳይባክን ትርፍራፊውን ሁሉ ሰብስቡ። በቃል ብቻ የሚቀር ልብን የማይነካ እምነት አለ፤ ይህ ዓይነቱ እምነት ወደ ተግባራዊ ኑሮ አይመጣም። ኃይማኖታዊ ኃላፊነቶችና በሥራ ረገድ የሚታዩት አብላጫ ያላቸው የሰው የአስተዋይነት መሥመሮች መጣመር አለባቸው። 2Manuscript, 31, 1897.AHAmh 277.2

  እራሳችሁን ክዳችሁ ክርስቶስን ተከተሉ፦ የሰው ልጅ ከሚገጥሙት ቅሬታዎች ፈተናዎችና ሐዘኖች ጋር በደንብ ይተዋወቅ ዘንድ ክርስቶስ ወደ ጥልቅ ስቃይና ውርደት ወረደ። ተከታዮቹ እንዲከተሉት የሚፈልግባቸውን መንገድ ራሱ ተራምዶታል። እንዲህ ይላቸዋል፡- “ራሱን ይካድ መስቀሉን ይሸከም።” ክርስቲያን ነን የሚሉቱ ግን አዳኙ የሚፈልገውን እራስን መካድ ሁልጊዜ ለመተግበር ፈቃደኛ አይደሉም። ለጌታ የበለጠ መስጠት ይችሉ ዘንድ ምኞታቸውንና ፍላጎታቸውን መቆጠብ አይፈልጉም። አንዱ እንዲህ ይላል “የቤተሰቤ ምርጫ በጣም ውድ ውድ ነገር ነው፤ የሚፈልጉትን ለማሟላት ብዙ ያስወጣል።” ይህ የሚያሳየው የክርስቶስ ሕይወት ያስተማረው የምጣኔ ሀብት አያያዝ ትምህርት እንደሚያስፈልጋቸው ነው....AHAmh 277.3

  እራስ-ወዳድና አባካኝ ፍላጎትን ለማርካት መፈለግ የሁሉም ፈተና ነው፤ ነገር ግን ለሰው ዘር እራስን የመካድ ትምህርት ለማስተማር ወደ ዓለም የመጣውን የሕይወትና የክብር ጌታ የሆነውን እናስታውሰው። 3Letter 4a, 1902.AHAmh 277.4

  ለራሳቸው ብቻ የማይኖሩ ሰዎች፣ ምናባዊ ፍላጎታቸውን ለማርካትና ምቾታቸውን ለመጠበቅ እያንዳንዱን ብር አያወጡም፤ የክርስቶስ ተከታይነታቸውን በማስታወስ ምግብና አልባሳት የሚፈልጉ ሌሎች እንዳሉ ያስተውላሉ። 4Review and Herald, Aug. 21, 1894.AHAmh 277.5

  የእግዚአብሔርን ዓላማ ለማሳካት ቆጣቢ ሁኑ፦ መሻትን የመግዛትንና የቆጣቢነትን ትምህርት በመማር ወጣቶች የእግዚአብሔርን እቅድ ለማገዝ ስላላቸው እድል ብዙ መናገር ይቻላል። ብዙዎች ደስ ሊላቸው እንደሚገባ በማሰብ ገቢያቸውን በሙሉ ለዚህ ዓላማ ማዋልን ይለማመዳሉ። ጌታ በዚህ ረገድ የተሻለ እንድናደርግ ይፈልጋል። የምንበላው፣ የምንጠጣውና የምንለብሰው በቂ ነገር አግኝተን ስንረካ (የምንፈልገው ነገር ይህ ብቻ ነው ብለን ስናስብ) በራሳችን ላይ ኃጢአት እንሠራለን። እግዚአብሔር ከዚህ የበለጠ ዓላማ በፊታችን አስቀምጧል። የራስ-ወዳድ ፍላጎቶቻችንን አሽቀንጥረን ጥለን፣ የልባችንና የአዕምሮአችን ጉልበት የእግዚአብሔርን ዓላማ ከጥግ ለማድረስ ስንጠቀምበት፤ ሰማያዊ ወኪሎች(ሠራተኞች) ከእኛ ጋር ይተባበራሉ፤ ለሰው ዘር ሁሉ በረከት እንድንሆንም ያደርጉናል።AHAmh 278.1

  ቆጣቢና ታታሪ የሆነ/ች ወጣት ምንም ድኃ ቢሆን/ብትሆን ለእግዚአብሔር ጉዳይ ትንሽ ማጠራቀም ይችላል/ትችላለች። 5The Youth’s Instructor, Sept. 10, 1907.AHAmh 278.2

  አላስፈላጊ በሆነ ወጪ በምትፈተኑበት ጊዜ፦ ለጥቃቅን የጌጣጌጥ ዕቃዎች ገንዘብ ለማውጣት ስትከጅሉ፣ በኃጢአት የወደቀውን ሰው ለማዳን ክርስቶስ ያለፈበትን እራስን የመካድና እራስን መስዋዕት የማድረግ ስቃይ አስታውሱ። ልጆቻችን ስለራስን መካድ፣ መሻትን መግዛትና እራስን መቆጣጠር መማር አለባቸው። ብዙ አገልጋዮች በገንዘብ ጉዳይ ላይ ፈታኝ ጊዜ የሚያሳልፉት ምርጫዎቻቸውን፣ ፍላጎቶቻቸውንና ዝንባሌዎቻቸውን ስለማይቆጥቡ ነው። ብዙ ወንዶች የሚከስሩት እንዲሁም ታማኝነት በጎደለው መንገድ ሀብት የሚሰበስቡት፤ የብክነት ኩይሣ የተቆለለበትን የሚስቶቻቸውንና የልጆቻቸውን ምርጫ ለማሟላት ሲጥሩ ነው። የምጣኔ ሀብት አያያዝን አስፈላጊነት በመመሪያነትና በምሣሌነት እናቶችና አባቶች ለልጆቻቸው ለማስተማር እንዴት ጥንቁቅ መሆን አለባቸው! 6Letter 11, 1888.AHAmh 278.3

  የእግዚአብሔርን ገንዘብ በብልጭልጭ ነገሮች ላይ የማጥፋት ከባድ ኃጢያተኛነትን በእያንዳንዱ አዕምሮ ማስቀመጥ በቻልኩ ብዬ ተመኘሁ። ጥቃቅን በሚመስሉ ነገሮች ላይ የሚወጣው ወጪ የተቀጣጠሉ ለዘለዓለም የሚዘልቁ ነገሮች መጀመሪያ ሊሆን ይችላል። ችሎት ሲሰየም፣ መጻሕፍት ሲገለጡ የጠፋው ነገር ወደ እይታችሁ ይመጣል፤ ባጠራቀማችኋቸው ሳንቲሞችና ባከማቻችሁት ሀብት በራስ-ወዳድ ዓላማችሁ ያጠፋችሁትን ሁሉንም ገንዘብ ለመልካም ብታውሉት ኖሮ ምን ማከናውን ይችል እንደነበር እንድታዩ ትደረጋላችሁ። 7Review and Herald, Aug. 11, 1891.AHAmh 278.4

  ሳንቲሞቻችሁን (the Pennies and Nickels) ተቆጣጠሩ፦ አላስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን በመግዛት ሳንቲሞቻችሁንና ሽልንጎቻችሁን አታባክኑ። እነዚህን ሳንቲሞች ብዙም ዋጋ ላትሰጧቸው ትችላላችሁ፤ ሲጠራቀሙ ግን በርካታ ገንዘብ ይሆናሉ። ብንችልስ ለአላስፈላጊ ነገሮች ለምናጠፋው፣ ለልብስና ለግል እርካታ ለምናወጣው ገንዘብ እንሟገት። ድህነት በተለያየ መልክ በሁሉም እጅ ላይ አለ። በቻልነው ሁሉ የሚቸገረውን የሰው ዘር ከስቃዩ እናላቅቀው ዘንድ እግዚአብሔር የእኛ ኃላፊነት አድርጎታል። AHAmh 278.5

  ሰዎች አሳቢና ጥንቃቄ የሚያደርጉ እንዲሆኑ እግዚአብሔር ይፈልጋል። በሁሉም ነገር ላይ ቆጣቢነትን እንዲተገብሩ ምንም እንዳያባክኑ ይፈልጋል። 8Letter 21, 1898AHAmh 279.1

  በየቀኑ ባላስፈለጊ ነገሮች ላይ የሚወጣው “አንድ ሳንቲም ነው” ወይም “አሥር ሳንቲም ብቻ እኮ ነው” የሚባለው አባባል በጣም ጥቂት ይመስላል። ነገር ግን እነዚህን ጥቃቅን ወጪዎች በዓመቱ ውስጥ ባሉት ቀናት አባዙት፤ ዓመታት እየተቆጠሩ ሲሄዱ የድምሩ ትልቅነት ለማመን የሚያቅት እውነት ይሆናል። 9Christian Temperance and Bible Hygiene, p. 63.AHAmh 279.2

  ፋሽን ከሚከተሉ ጎረቤቶቻችሁ ጋር አትወዳደሩ፦ ሀብታም መስሎ መታየትና ከእውነታው በላይ እንደሆንን ማስመሰል መልካም አይደለም፤ ትሁቶች የሆንን የየዋሁና ዝቅ ያለው አዳኝ ተከታዮች ነንና። እኛ እንከተለው ዘንድ በማይገባን መልኩ ጎረቤቶቻችን ሕንፃ ቢገነቡ ቤቶቻቸውን በእቃ ቢሞሉ ልንረበሽ አይገባንም። ራስ-ወዳድነታችንንና ሆዳምነታችንን ለማርካት ስናጋብስ እንግዶቻችንን ለማስደሰት ወይም የራሳችንን ዝንባሌዎች ለማሟላት ስንሮጥ፣ ክርስቶስ እንዴት ይመልከተን! ራሳችን ወይም በቁጥጥራችን ሥር ያሉ ልጆቻችን የታይታ ሥራ ላይ እንዲገኙ ብንፈቅድ በራሳችን ላይ ወጥመድ እንዘረጋለን። 10Letter 8, 1889.AHAmh 279.3

  ሚስስ ዋይት በኮረዳነትዋ የነበራት ልምድ፦ ገና አሥራ ሁለት ዓመት ልጅ እያለሁ እንዴት መቆጠብ እንዳለብኝ አውቅ ነበር። ከእህቴ ጋር ንግድ ተማርሁ፤ በቀን የምናገኘው ሃያ አምስት ሳንቲም ቢሆንም ለሚሲዮናዊ ሥራ ትንሽ ትንሽ እያጠራቀምን እንሰጥ ነበር። ስናጠራቅም፣ ስናጠራቅም ሰላሳ ዶላር ደረሰችልን። የጌታ በቶሎ የመመለሱ መልእክት ሲደርሰን፣ የሚሠሩ ሰዎችና ገንዘብ እንደሚያስፈልግ ስናውቅ ትንንሽ በራሪ ጽሑፎችን (Tracts & pamphlets) በመግዛት መልእክቱ በጨለማ ላሉ ይደርስ ዘንድ እንዲያውለው ሰላሳ ዶላሩን ለአባታችን ሰጠነው….AHAmh 279.4

  በንግድ ሥራ በምናገኘው ገንዘብ ለእኔና ለእህቴ አልባሳት ገዛን። ገንዘቡን ለእናታችን ስንሰጣት እንዲህ እንላት ነበር፡- “ለሚሲዮናዊ ሥራ ትንሽ እንዲተርፍ አድርገሽ ልብስ ግዢልን።” ያገልግሎት መንፈስ በውስጣችን እንዲበረታታ እናታችን ይህንን ታደርገው ነበር። 11The Youth’s Instructor, Sept. 10, 1907.AHAmh 279.5

  ቆጣቢነትን ከመርህ ተማሩ፦ የእግዚአብሔር ሥራ በቋሚነት እንዲቀጥል ለማድረግ ለሚወጣው ጥሪ እጃቸውን የሚዘረጉ፣ ለችግረኞችና ለድኆች የሚለግሱ እነርሱ በንግድ ሥራ አመራር ልል፣ ግድ-የለሽና ቀርፋፋዎች አይደሉም። ወጫቸው ገቢያቸውን ያገናዘበ እንዲሆን ሁሌም ጥንቁቅ ናቸው። ቆጣቢነትን ከመርህ ያገኙ ናቸው፤ የሚለግሱት ነገር ይኖራቸው ዘንድ የመቆጠብ ኃላፊነት እንዳለባቸው ይሰማቸዋል። 12Testimonies for the Church, Vol. 4, p. 573.AHAmh 280.1