ምዕራፍ ሃያ ሁለት—ቤትን መሥራትና በዕቃ ማሟላት
ቤት የአየር መዘዋወሪያና የፀሐይ ብርሃን መግቢያ ይኑረው፦ ለሕዝብም ሆነ ለግል መኖሪያ የህንፃ ግንባታ በሚካሄድበት ጊዜ፣ ጥሩ የአየር መናፈሻ እንዲበጅለትና በቂ የፀሐይ ብርሃን እንዲያገኝ ጥንቃቄ መደረግ አለበት። ቤተ-ክርስቲያንና የትምህርት ቤት ክፍሎች በዚህ ረገድ ችግር አለባቸው። በቂ አየር እንዲዘዋወር የሚያደርግ አሠራርን ቸል ማለት በቤተ-ክርስቲያን ውስጥ ለብዙ ሰዎች መፍዘዝና ማንጎላጀት ብሎም ጥቂት የማይባሉ ስብከቶች መልዕክቶች ከንቱ እንዲቀር ሲያደርግ በትምህርት ቤት ደግሞ የመምህሩ ልፋት ዋጋ-ቢስ እንዲሆን ምክንያት ነው።AHAmh 98.1
በተቻለ መጠን ለሰዎች መኖሪያ የታቀዱ ግንባታዎች ሁሉ፣ በከፍታማና ፍሳሽ በደንብ መውረድ በሚችልበት ቦታ መቀመጥ አለባቸው። ይህም ቦታው ደረቅ እንዲሆን ያደርጋል….. ይህ ጉዳይ ብዙ ጊዜ እንደ ቀላል ታይቶ የሚታለፍ ነው፤ ተደጋጋሚ የጤና ችግር፣ አደገኛ በሽታዎች እንዲሁም ብዙ ሞት የሚከሰተው እርጥበትና ወባ ባለበት ረባዳና ፍሳሽ ተንጠፍጥፎ በማይወርድበት ቦታ ነው። ቤት ሲገነባ ጥሩ አየር የሚናፈስበትና የፀሐይ ብርሃን በብዛት የሚያርፍበት መሆኑ እጅግ አስፈላጊ ነው። በእያንዳንዱ ክፍል የሚዘዋወር አየርና በቂ የፀሐይ ብርሃን መኖር አለበት። የመኝታ ክፍሎች በቀንም ሆነ በሌሊት ነፃ የአየር ዝውውር እንዲኖራቸው ሆነው መዘጋጀት ይኖርባቸዋል። ለአየርና ለፀሐይ ብርሃን ተከፋፍቶ መዋል የማይችል ክፍል ለመኝታነት ብቁ አይደለም። በብዙ አገራት እንደሚያስፈልገው ሁሉ የመኝታ ክፍሎች ለማሞቂያ እንደሚመቹ ሆነው በእርጥብ ወይም በቀዝቃዛ የአየር ንብረት ወቅት በደንብ መሞቅና መድረቅ አለባቸው።AHAmh 98.2
የእንግዳ ማረፊያዎችም ሁልጊዜ እንደሚተኛባቸው ክፍሎች እኩል ጥንቃቄ ያስፈልጋቸዋል። እንደ ሌሎች የመኝታ ክፍሎች ሁሉ በቂ አየርና የፀሐይ ብርሃን ያስፈልጋቸዋል፤ በአብዛኛው የማይተኛበት ክፍል ሁልጊዜ እርጥበት ስለሚጠራቀምበት ሊያደርቀው የሚችል ማሞቂያ ሊዘጋጅለት ይገባል። የፀሐይ ብርሃን በማይደርስበት ወይም በበቂ ሁኔታ ባልደረቀና አየር በማይዘዋወርበት ክፍል የሚተኛ ሰው በጤናውና በሕይወቱ ፈርዶ ይተኛል…. ሽማግሌዎችን የሚንከባከቡ (የሚጦሩ) ደግሞ ክፍሎቻቸው በተለየ ሁኔታ መሞቅ እንዳለባቸው ማስታወስ አለባቸው። ዕድሜ ሲገፋ ጉልበት ይደክማል፤ ጤናማ ያልሆኑ ነገሮችን ለመቋቋም ጥንካሬ ያንሳቸዋል። ስለሆነም በዕድሜ ለገፉ ሰዎች ብዙ የፀሐይ ብርሃን ትኩስና ንጹህ አየር በበለጠ ያስፈልጋቸዋል።AHAmh 98.3
ረባዳ ቦታዎችን አትምረጡ፦ ቤቶቻችን የጤናና የደስታ መኖሪያ እንዲሆኑ ከፈለግን፣ ሕይወት ሰጪ ሰማያዊ ወኪሎች በነፃነት እንዲገቡ ካሰብን፣ መጥፎ የአየር ጠባይና ጉም ከበዛባቸው ዝቅተኛ ቦታዎች በላይ ከፍ ብለን ቤቶቻችንን መሥራት አለብን። ወፋፍራም መጋረጃዎችን አስወግዱ፤ ስስ የውስጥ መጋረጃዎችን ገልጣችሁ መስኮቶቹን ክፈቱ። ምንም ውብ ቢሆኑ እንኳን መስኮቶችን የሚጋርዱ የወይን ተክሎች አይኑሩ፤ ከቤቱም በጣም የቀረቡ የፀሐይ ብርሃን የሚጋርዱ ዛፎች አያስፈልጉም። የፀሐይ ብርሃን መጋረጃዎችንና ምንጣፎችን ሊያደበዝዝ፣ ፎቶ ፍሬሞችንም ሊያጠቁር ይችላል፤ ነገር ግን ጤናማ ፍካት ወደ ልጆች ጉንጮች የሚያመጣ ነው።AHAmh 99.1
ቤቱን የከበበው አጥር ግቢ፦ ከቤቱ የተመጣጣነ ርቀት ባላቸው በተበታተኑ ዛፎችና የተወሰኑ ቁጥቋጦዎች የተዋበ ግቢ ለቤተሰቡ ደስታ የሚያስገኝ ነው፤ ግቢው ጥሩ እንክብካቤ ከተደረገለት ለጤና ጎጅ አይሆንም። የተቀራረቡ ጥቅጥቅ ያሉ ዛፎችና ቁጥቋጦዎች ከቤቱ ተጠግተው መኖራቸው ነጻ የአየር ዝውውርና የፀሐይ ጮራ ስለሚጋርዱ ጤናማ አይደሉም። በተለይ ፍሳሽ በሚበዛበት ወቅት እርጥበት በቤት ውስጥ እንዲጠራቀም ያደርጋሉ።AHAmh 99.2
ተፈጥሮአዊ ውበት በቤተሰብ ላይ ያለው ተጽዕኖ፦ እግዚአብሔር ውብ የሆነን ነገር ይወዳል። ምድርና ሰማያትን ውበት አለበሳቸው፤ በሠራቸው ነገሮች ልጆቹ ሲደሰቱ ሲመለከት ደስ ይሰኛል። ተፈጥሮአዊ የሆነ ውበት ቤታችንን እንዲከበው ይፈልግብናል። በገጠር ያሉ አብዛኛዎቹ ነዋሪዎች ድኃ የሆኑት እንኳ ጭምር በቤታቸው ዙሪያ ትንሽ የሳር መስክና ጥላ ያላቸው አበቦች ሊኖሯቸው ይችላል። ከማንኛውም ሰውሰራሽ ጌጥ በበለጠ ለቤተሰቡ ደስታ የሚለግሱ ይሆናሉ። እነዚህ ዕፅዋት ለቤት ውስጥ ኑሮ ለስለስ የሚያደርግና የሚያነፃ ተጽዕኖ በማምጣት እርስ በእርሳቸው እንዲቀራረቡ ወደ እግዚአብሔርም የበለጠ እንዲጠጉ ይረዳሉ።AHAmh 99.3
የቤት ዕቃዎች ቀለል ያሉ(ውድ ያልሆኑ) ይሁኑ፦ ሰው ሠራሽ የሆነው ልምዳችን ብዙ በረከቶችና ደስታን ያሳጣናል፤ ጠቃሚ የሆነ ሕይወት ለመኖርም ብቁ ሳንሆን እንቀራለን። የሚያማምሩና ውድ የሆኑ የቤት ዕቃዎች ገንዘብን ብቻ ሳይሆን ከሺህ እጥፍ የሚበልጠውን የከበረ ነገር የሚያባክኑ ናቸው፤ ለውድ ዕቃዎች ሲባል የሚያስፈልገውን ከባድ የጥንቃቄ የድካምና የመደነጋገር ሸክም ወደ ቤት የሚያመጡ ናቸው….AHAmh 99.4
ቻይ በሆኑ በቀላሉ መጽዳት በሚችሉና ለመቀየርም ብዙ ገንዘብ በማያስወጡ ቀላልና ጌጥ ባልበዛባቸው ዕቃዎች ቤታችሁን አሟሉ። እርካታና ደስታ እስከሰጧችሁ ድረስ ምርጫዎቻችሁን በማስተካከል የሚጋብዝና የሚስብ፣ ያልተወሳሰበ ቤት እንዲኖራችሁ ማድረግ ትችላላችሁ።AHAmh 99.5
በባዶ ትዕይንት ደስታ አይገኝም፤ ቀላልና ሁሉም ነገር ሥርዓት የሰፈነበት ቤት - ያ ነው የበለጠ ደስታ ያለበት።AHAmh 100.1
የፉክክርን መንፈስ አስወግዱ፦ ባህል የሚጠይቀውን ለማሟላት ሲሉ በአላስፈላጊ ልፋት ለራሳቸው ሸክም በማብዛታቸው ሕይወት ለብዙዎች የቅሬታና የድካም ኑሮ ሆኖባቸዋል። ኩራትና ፋሽን የወለዳቸውን ፍላጎቶች ለማሟላት ሲማስኑ ሁልጊዜ አዕምሮአቸውን በጭንቀት ያሰቃዩታል….AHAmh 100.2
ብዙ ወጪ ጥንቃቄና ድካም የፈሰሰበት አላስፈላጊ የሆነ ዕቃ ጉዳት ባያስከትል እንኳን ጠቃሚ በሆነ ነገር ላይ ቢውል ኖሮ የእግዚአብሔርን ዓላማ ለማስፈፀም መዋል ይችል ነበር። የሕይወት ድሎት ናቸው ለሚባሉ ነገሮች ሰዎች ይራባሉ፤ ለማግኘትም ሲሉ ጤናቸውን፣ ጉልበታቸውንና ሀብታቸውን ይሰዋሉ። በተመሳሳይ የኑሮ ደረጃ የሚኖሩ ሰዎች ማንኛቸው የበለጠውን የቤት ወጪ እንዳወጡና ከሁሉም የተሻለ ልብስ እንደለበሱ ለማሳየት አሳዛኝ የሆነ የፉክክር መንፈስ ውስጥ ገብተዋል። በተለያዩ የሕይወት ጓዳዎች እየደከሙ ባሉበት ሰዓት የባህልን ጥያቄዎች ለማሟላት ሲሉ በሚሰበስቡት ኮተት ምክንያት “ቤት” የሚለው ጣፋጭ ቃል ተጣምሞ “አራት ማዕዘን ያለው በድንቃድንቅ ዕቃዎችና ማስጌጫዎች የተሞላ መጋዘን” በሚለው ተተክቷል።AHAmh 100.3
የገዟቸውን ውድ ዕቃዎች ገጽታ ጠብቆ ለማቆየት በሚያደርጉት ያላሰለሰ ጥረት ብዙዎች በቤታቸው ደስተኞች አይደሉም። የእዩኝ እዩኝ ገጽታን በማንፀባረቅ በጓደኞቻቸው አድናቆት ያተርፉ ዘንድ ያለማቋረጥ ብዙ ገንዘብና ጉልበት ያወጣሉ - ለእነርሱ ወይም ለብልጽግናቸው ምንም ግድ በማይላቸው ጓደኞቻቸው ለመሞገስ። ብዙ ውድ የሆኑ ዕቃዎች በቤት ውስጥ እስኪጠራቀሙ ድረስ ይህ ዕቃ መቅረት የለበትም፣ ያኛው እጅግ ጠቃሚ ነው እየተባሉ ይሰበሰባሉ። ለዐይን ያስደስቱ ይሆናል፤ ትምክህትንና ኩራትን ያረኩ ይሆናል፤ የቤተሰቡን ምቾት ግን አንዲት ቅንጣት አይጨምሩለትም። እነዚህ ነገሮች ጉልበትና ትዕግሥት የሚያሟጥጡ፣ ለእግዚአብሔር ሥራ የሚውለውን ውድ ጊዜ የሚወስዱ ናቸው።AHAmh 100.4
የከበረውና ዋጋ የማይገኝለት የእግዚአብሔር ፀጋ እውነተኛ ጥቅም በሌላቸው ጉዳዮች ተተክቶ ሁለተኛ ደረጃ ይሰጠዋል። ብዙዎች ሐሴት ለማግኘት ሲሉ ቁሳዊ ነገርን ሲሰበስቡ የመደሰት ብቃታቸውን ያጣሉ። እናገኛለን ብለው ተስፋ የሚያደርጉትን እርካታ በሰበሰቧቸው ነገሮች ማግኘት ይሳናቸዋል። ይህ ማለቂያ የሌለው ልፋት፤ ይህ በጎብኝዎችና በእንግዶች ቤቶቻቸው እንዲደነቁላቸው የማስዋብ የማያቋርጥ ጭንቀት፤ ሙገሳውና አድናቆቱ ሊገኝ ቢችል እንኳ የወጣበትን ገንዘብና ጊዜ ፈጽሞ ሊተካ የሚችል አይደለም። ሊሸከሙት አደገኛ የሆነ ሸክም በአንገት ዙሪያ መጠምጠም ነው።AHAmh 100.5
ያወዳደርናቸው ሁለት ጉብኝቶች፦ በአንዳንድ ቤተሰቦች ደግሞ ከመጠን ያለፈ ሥራ ይሠራል። ሥርዓትና ንጽህና ለምቾት አስፈላጊ ቢሆኑም እንኳን ከሚገባው በላይ በመተግበር ሕይወትን ማማሰንና በማያቋርጥ ልፋት ቤት ውስጥ ያሉትን ሁሉ አሰቃቂ ማድረግ ተገቢ አይደለም። በአንዳንድ በጣም በምናከብራቸው ሰዎች ቤት አላስፈላጊ የሆነ ጥንቁቅነት በዕቃዎች አቀማመጥና በሁሉም ነገር ላይ ይታያል። ልክ በዝርክርክነት የማንስማማውን ያህል በእንደዚህ ዓይነቱ ወግ አጥባቂነትም አንስማማም። ቤቱን የሞላው የሚያቆስል ሥነ-ሥርዓት ከእውነተኛ ቤት መገኘት የሚገባውን ዕረፍት የሚያሳጣ ነው።AHAmh 101.1
ለመጎብኘት ሲኬድ አሁንም ቅድምም መጥረጊያውንና መወልወያውን ማንሣት ደስ የሚል ነገር አይደለም። እናንተ ከጓደኞቻችሁ ጋር ልትደሰቱና ልትጫወቱ አስባችሁ ሄዳችሁ እነርሱ የተለያየ ነገር ሲያጸዱ አጣብቂኝ ቦታዎች አካባቢ ትኩር ብለው እየተመለከቱ የተደበቀ ጉድፍና የሸረሪት ድር በማጥራት ጊዜውን ሲገድሉት የሚያስከፋ ሊሆን ይችላል። ይህንን የሚያደርጉት በቤታቸው በመገኘታችሁ ለእናንተ ክብር ሲባል ሊሆን ይችላል፤ ሆኖም ከእናንተ አብሮነት ይልቅ ለቤታቸው ከመጠን ያለፈ ንጽሕና ቦታ እንደሚሰጡ ማየታችሁ መጥፎ ስሜት እንዲያድርባችሁ ሊያደርግ ይችላል።AHAmh 101.2
ከእነደዚህ ዓይነት ቤቶች በተቃራኒው ባለፈው በጋ(1876) የጎበኘነው አንድ ቤት ነበር። እዚህ ያጠፋናቸው ጥቂት ሰዓታት በከንቱ ድካም ወይም ሌላ ጊዜ ሊሠሩ በሚችሉ ነገሮች ላይ አልነበረም። የሚያስደስትና ትርፋማ ጊዜ ነበር፤ አዕምሮአችንና ሰውነታችን በእኩል ዕረፍት አግኝቶ ነበር። ብክነት በሚያሳዩ የቤት ዕቃዎች ባይሞላም ቤቱ የዕረፍት ምሣሌ ነበር። ሁሉም ክፍሎች በቂ ብርሃን ያላቸውና አየር የሚዘዋወርባቸው ነበሩ…. ውድ ከሆኑ ማስጌጫዎች ሁሉ የበለጠ ዋጋ ያላቸው ናቸው። የማረፊያ ክፍሎቹ ለዐይን በሚያደክም ሁኔታ ዝንፍ ሳይሉ በተቀመጡ ቁሳቁሶች ባይሞሉም የተለያዩ የሚያስደስቱ እቃዎች ግን ነበሩበት። አብዛኛዎቹ ወንበሮች ተወዛዋዥና ቀላል ሆነው አንድ ዓይነት ግን አልነበሩም። የተለያየ የአካል መጠን ላላቸው የቤተሰቡ አባላት እንዲመቹ ሆነው የተሠሩ ነበሩ። ትራስ ያላቸው ከፍና ዝቅ ያሉ የሚወዛወዙ ወንበሮች፤ ቀጥ ያለ መደገፊያ ያላቸው መቀመጫዎች፤ ሰፊና ብዙ ቦታ ያላቸው የመዝናኛ ወንበሮች፤ ትናንሽና ምቹ ወንበሮችም ነበሩ። የሚመቹ ሶፋዎች ነበሩበት፤ ሞክሩኝ፣ እረፉብኝ የሚሉ ይመስላሉ። ሁሉም ንፁህና ማራኪ ነበሩ፤ ነገር ግን ከመጠን ባለፈ ጥንቁቅነት የተደራጁ፣ እንዳይዛነፉ በመስጋት ለመንካት በሚያስፈራ ሁኔታ የተቀመጡ አልነበሩም።AHAmh 101.3
የዚህ ቤት ባለቤቶች ቤታቸውን እጅግ ውድ በሆኑ የቤት ዕቃዎች የማስጌጥ አቅም ነበራቸው፤ ነገር ግን ከታይታ ምቾትን መርጠዋል። እዚህ ቤት ውስጥ ከውድነታቸው የተነሣ የየዕለት ተግባርን ለማከናወን ሲባል ለመንካት የሚያሳሱ እቃዎች አልነበሩም፤ የቤት እቃዎች እንዳይጎድፉና በፀሐይ ብርሃን ምክንያት ምንጣፉ ቀለሙን እንዳይቀይር በማሰብ የላይኛውም ሆነ የሥረኛው መጋረጃዎች ግጥም ብለው የተዘጉ አልነበሩም። በአትክልት ሥፍራው ካሉት የአበቦች መዓዛ ጋር እግዚአብሔር የሰጣቸው የፀሐይ ብርሃንና አየር ዘው ብሎ የመግባትና የመዘዋወር ነፃነት ነበረው። በእርግጥ የቤቱ ትኩረት ቤተሰቡ ነበር፤ አዝናኝና ደስ የሚያሰኙ ለምቾታችን መጠበቅ አስፈላጊውን ሁሉ ያደረጉ፤ ያለመጠን ትኩረት በማግኘት ችግር እየፈጠርን እንደሆነ ተሰምቶን እንዳንሳቀቅም ያደረጉን ነበሩ። የዕረፍት ቦታ ማለት ይህ እንደሆነ ተሰማን። ቤት የሚለውን ቃል ትርጉም ሙሉ ለሙሉ የተገበረ ቤት ነበረ።AHAmh 102.1
የማስጌጥ መርህ፦ ቀደም ብለን የጠቀስነው የማንስማማበት አላስፈላጊ የሆነ ግትር ጥንቁቅነት በብዙ ቤቶች የሚታይ ቢሆንም ቅሉ እንደ ታላቁ የተፈጥሮ እቅድ ግን አይደለም። በመስክ ላይ ያሉትን አበቦች እግዚአብሔር በአንድ መደብ ሆነው ድንበር አብጅቶላቸው እንዲያድጉ አላደረገም፤ በተለያየ ቅርፃቸውና ቀለማቸው ምድርን ያስውቡ ዘንድ እንደ ከበሩ ድንጊያዎች በለመለመው መስክ በተናቸው። በጫካ ያሉት ዛፎች በመሥመር የተተከሉ አይደሉም። የተፈጥሮን ገፅታ መመልከት ለዐይንና ለአዕምሮ ዕረፍት ነው፤ ከደኑ ባሻገር ኮረብታውን፣ ሸለቆውን፣ ሜዳውንና ወንዙን ሊቆጠር በማይችል የተለያየ ቅርጽና የቀለም ስብስብ የተቀባውን እንዲሁም ዛፎች ቁጥቋጦዎችና አበቦች በተፈጥሮ የአትክልት ቦታ የተሰበሰቡበትን ስፍራ ማየት ልዩ ትዕይንትን ይፈጠራል።AHAmh 102.2
ይህ የዓይነት(variety) ሕግ በተወሰነ መልኩ በቤትም ሊተገበር ይችላል። የቤት ዕቃ በሚሟላበት ጊዜ የቀለሞች መጣጣምና የነገሮች በልክ በልክ መሆን ጥሩ ነው። ሆኖም ደስ የሚያሰኝ ለመሆን በእያንዳንዱ ክፍል ያለው የቤት ዕቃ ተመሳሳይ የሆነ ቅርጽና ስሪት እንዲሁም ወንበሮች መጋረጃዎች ስጋጃዎችና የመሳሰሉት ግዴታ አንድ ዓይነት መሆን የለባቸውም፤ በተቃራኒው የተለያዩ ሆነው ግን የተዋሐዱ ቢሆኑ የበለጠ ለዕይታ ደስ ይላል።AHAmh 102.3
ቤቱ ተራም ይሁን ያሸበረቀ፣ ውድ ዋጋም ባላቸው ዕቃዎች ይሞላ ወይም በተቃራኒው፣ የነዋሪዎቹ መንፈስ ከመለኮታዊ ፈቃድ ጋር ካልተስማማ በዚያ ጣራ ሥር ደስታ ሊኖር አይችልም።AHAmh 102.4
ከሁሉም የሚመቸው የቤቱ ክፍል፣ ማለትም ፀሐያማና ከሌሎች በተሻለ ደስ የሚያሰኙና የሚጋብዙ ክፍሎች፣ እንዲሁም ምቾት የሚሰጡ የቤት ዕቃዎች ተከብክበው ለእይታ መቀመጥ ሳይሆን በቤት ውስጥ በሚኖሩ ሰዎች ዕለት ተዕለት ጥቅም ላይ መዋል አለባቸው። ይህ ቤትን ለነዋሪዎቹ ማራኪ ያደርገዋል፤ በተጨማሪም በሚጠነቀቁልን፣ በምንጠቅማቸውና በሚጠቅሙን ጓደኞቻችን ዘንድ ቤታችንን ተወዳጅ ያደርገዋል።AHAmh 102.5
ለልጆች ምቾትና ደህንነት ተጠንቀቁ፦ ልጆች ደስተኛ እንዲሆኑና እርካታ እንዲያገኙ ከተፈለገ ወጪ የበዛበት አካባቢና ውድ የሆኑ የቤት ዕቃዎች ማሟላት አስፈላጊ አይደለም። ሆኖም ወላጆች ጣፋጭ ፍቅርና ልዩ ትኩረት ሊለግሷቸው ይገባል።AHAmh 103.1
አራት ማዕዘን ያላቸው ግድግዳዎችና ውድ የቤት ዕቃዎች፣ ከሐር የተሠሩ ምንጣፎች፣ ያሸበረቁ መስታውቶችና ውብ ፎቶዎች የሞሉበት መኖሪያ ርኅራኄና ፍቅር ከሌለበት “ቤት” ሊሆን አይችልም። ያ የተቀደሰው ቃል [“ቤት”]፣ የቤት ውስጥ ሕይወት ደስታ ምን እንደሚመስል የማይታወቅበት አስገራሚ ውጫዊ ውበት የተላበሰ እልፍኝ አይደለም….AHAmh 103.2
እንዲያውም የዚህ ዓይነት ቤት ለልጆች ምቾትና ደህንነት የመጨረሻውን ደረጃ የያዘ ነው። ለታይታ ቦታ ከሚሰጥና ፋሽንን ከሚከተል ማህበረስብ ጋር እኩል ለመሆን በምታደርገው ጥረት ጊዜዋን ሁሉ ስለምታጠፋ እናት ልጆችዋን ችላ ትላቸዋለች። አዕምሮአቸው አይሠለጥንም፤ መጥፎ ልምዶችን ያጎለብታሉ፤ ዕረፍት-የለሽና የማይረኩ ይሆናሉ። በቤታቸው የሚያገኙት የማይመቿቸውን ቁጥጥሮች እንጂ ደስታን ስላልሆነ በሚችሉት ፍጥነት ከቤተሰቡ ክበብ መለየትን ይሻሉ። የቤተሰቡ ሕይወት መልካም ምሣሌ ሳይሆንላቸው፣ በቤት ተጽዕኖ ሳይገደቡ፣ ያለምንም ማቅማማት ወደ ታላቁ ጨካኝ ዓለም ራሳቸውን ይወረውራሉ።AHAmh 103.3
ብዙ እናቶች ሲናገሩ እንደሰማሁት እንደዚህ አትበያቸው:- “በማረፊያ ሥፍራው ለእናንተ ቦታ የለም። በለስላሳ ሐር ከተሸፈነው ሶፋ ላይ እንዳትቀመጡ።” ወደ ሌላ ክፍል ሲሄዱ ደግሞ “እዚህ ጫጫታችሁን አልፈልግም” ይባላሉ። ወደ ወጥ ቤት ሲገቡ ደግሞ ምግብ አብሳይዋ “እዚህ በእናንተ መጨናነቅ አልፈልግም፤ ከጫጫታችሁ ጋር ከዚህ ውጡ፤ አትነዝንዙኝ” ትላቸዋለች። ትምህርት ለማግኘት ወዴት ይሂዱ? ወደ ጎዳና!AHAmh 103.4
ቸርነትና ፍቅር ከምቾት የበለጠ የከበረ ዋጋ አላቸው፦ ብዙ ችግሮችና ሸክሞች ከውጭ ወደ ቤተሰቦቻችን ይመጣሉ። ቀለል ያለ አኗኗር ሠላምና ደስታ ግን ዋጋ አይሰጣቸውም። የውጪው ዓለም ምን ይል ይሆን ብለን ከምንጨነቅ፣ በቤተሰቦቻችን ዙሪያ ስላሉት ነገሮች ትኩረት ብንሰጥ ይበጀናል። በዓለማዊ ትህትና ከመውደድና ከማስመሰል ይልቅ የበለጠ የዋህነትና ፍቅር፣ ደስተኝነትና ክርስቲያናዊ ደግነት በቤተሰቡ አባላት ሊበዛ ይገባዋል። ብዙዎች ቤት እንዴት ማራኪና የደስታ ቦታ መሆን እንደሚችል ገና ስላላወቁ መማር ይገባቸዋል። አመስጋኝ ልቦችና ደግ (የዐይን) አስተያየቶች ከሀብትና ምቾት የበለጠ ዋጋ አላቸው። ፍቅር ካለ በተራ ነገሮች በመርካት ቤት በደስታ ሊሞላ ይችላል።AHAmh 103.5
አዳኛችን የሱስ አንድ ንጉሥ የሚያንፀባርቀውን ክብር በማሳየት ምድር ላይ ተመላለሰ፤ ሆኖም የዋህና የተዋረደ ልብ ያለው ነበር። ደስታን፣ ተስፋንና ብርታትን ተሸክሞ ስለነበር ለገባበት ቤት ሁሉ ብርሃንና በረከት ነበር። ኦ! በመጠነኛ የልብ መሻት ብንረካ፣ ቤታችንን ለማስዋብ ስንል የምናሳድዳቸው ነገር ግን ልናገኛቸው በሚከብዱን ነገሮች ላይ ልፋታችንን ብንቀንስ፣ እንዴት መልካም በሆነልን ነበር! ሆኖም የሚያሳዝነው ግን እግዚአብሔር ከብርና ከወርቅ አስበልጦ ዋጋ የሚሰጣቸው እንደ የዋህነትና የተረጋጋ መንፈስ ያሉ ባህርያት በእኛ ዘንድ ቦታ የላቸውም። ቀላል የመሆን፣ የየዋህነትና የእውነተኛ ፍቅር ፀጋ ፈጽሞ ተራ የሚባለውን ቤት ገነት የሚያደርግ ነው። ከሠላምና እርካታ ጋር ከመለያየት እያንዳንዱን ችግር በደስታ መጋፈጥ ይሻላል።AHAmh 104.1