ምዕራፍ ሠላሳ ዘጠኝ—የእናት ተጽዕኖ
የእናት ተጽዕኖ ዘለዓለማዊ ነው፦ የእናት ወሰንዋ ጠባብ ሊሆን ይችላል፤ ተጽዕኖዋ ግን ከአባት ጋር ተዳምሮ ለዘለዓለም የሚኖር ነው። እናት ለመልካም ነገር ያላት ተጽዕኖ ከእግዚአብሔር ቀጥሎ በም ድር ላይ ተወዳዳሪ የሌለ ው ነው። AHAmh 167.1
የእናት ተጽዕኖ የማይቋረጥ ኃይል ያለው ነው። ሁልጊዜም በትክክለኛው አቅጣጫ ከሆነ ለግብረ-ገብነትዋ እውነተኛነትና ጠቀሜታ የልጆችዋ ባህርይ ይመሰክራል። ፈገግታዋና ማበረታቻዋ የማነቃቂያ ኃይል ነው። በፍቅር ቃልና በአዎንታዊ ፈገግታ ወደ ልጆችዋ ልብ ዘልቃ መድረስ ትችላለች….AHAmh 167.2
ተጽዕኖዋ ለእውነትና ለደግነት ከሆነ በመለኮታዊ ጥበብ ስትመራ ሕይወትዋ ለክርስቶስ እንዴት ዓይነት ኃይል ይሆን! ተጽዕኖዋም ለዘመናትና ለዘለዓለም ይዘልቃል። ምን ዓይነት የሚደንቅ ኃሳብ ነው፡- የእናት አስተያየት ቃላትና ድርጊቶችዋ የዘለዓለም ፍሬ ያዝላሉ፤ የብዙዎቹ መዳን ወይም መጥፋት የተጽዕኖዋ ውጤት ነው! AHAmh 167.3
ልጆችዋን በብልሃት የምታሠለጥን እናት ተጽዕኖዋ በምን ዓይነት ኃይል በሕይወት ውጣ ውረድ ውስጥ አልፎ ወደ ፊት ተዘርግቶ እስከ ዘለዓለማዊ ሕይወትዋ ድረስ እንደሚደርስ ብዙም ልብ አትለውም። በሰማያዊ ምሣሌ ልጆችን መቅረጽ እጅግ ታማኝነትን፣ ሀቀኝነትንና ያላሰለሰ ልፋትን ይጠይቃል። ሆኖም በእጅጉ ይክሳል፤ ነፍስን ለማዳን ለሚደረግ ለመልካም ተግባር እግዚአብሔር ሽልማት አለው። AHAmh 167.4
ልጆች እናታቸውን ይመስላሉ፦ ፈጽሞ ወደር የማይገኝለት የለመለመው ግንኙነት በእናትና በልጅ መካከል ያለው ነው። ከአባቱ ይልቅ ልጅ በእናቱ ሕይወትና ምሣሌነት በቀላሉ ይማረካል፤ ከአባት የበለጠ ጠንካራ የሆነ የሚያቆራኛቸው አንድነት አላቸውና። AHAmh 167.5
የእናት ሐሳብና ስሜት ለልጅዋ በምታወርሰው ቅርስ ላይ ከባድ ተጽዕኖ ይኖረዋል። አዕምሮዋ ለራስዋ ስሜት እንዲገዛ ከፈቀደችለት፤ የራስዋን ፍላጎት የምታረካ ከሆነች፤ ብስጩና በቃኝ የማትል ከሆነች፤ የልጅዋ ጠባይ ማንነትዋን ይመሰክራል። በመሆኑም ብዙዎች ለማሸነፍ የማይቻል የሚመስል የክፋት ዝንባሌ እንደ ብኩርና ከእናታቸው ወርሰዋል። ይህንን ጉዳይ ብዙ ወላጆች ከሚረዱት በተሻለ መረዳት የነፍስ ጠላት የበለጠ ያውቀዋል። የእናት ብቸኛ ተስፋ እግዚአብሔር ነው። ለብርታትና ፀጋ ወደ እርሱ ትሩጥ፤ ሩጫዋ በከንቱ አይቀርም። AHAmh 167.6
ክርስቲያን እናት ልጆችዋን የከበባቸውን አደጋዎች ለማወቅ ምንጊዜም ሙሉ በሙሉ የነቃች ናት። የራስዋን ነፍስ በንፁህና በቅዱስ ሥፍራ ታስቀምጣለች፤ መርሆዎችዋንና ጠባይዋን በእግዚአብሔር ቃል መሠረት በመቆጣጠር ሁልጊዜ ከሚነቁሩአት ከጥቃቅኖቹ ፈተናዎች በላይ በመኖር ሥራዎችዋን በታማኝነት ትፈጽማለች። AHAmh 168.1
የታጋሽ እናት የግብረ-ገብነት ተጽዕኖ፦ አንዱ ሲያለቅስ ሌላኛው እማማ እማማ እያለ ሲጠራት ቀኑን ሙሉ ስትርመሰመስ ትውላለች፤ ለለቅሷቸው መልስ ለመስጠት እናት ከአንዱ ልጅ ወደ ሌላው ትራወጣለች። አንደኛው በችግር ላይ በመሆኑ ከግራ መጋባቱ ለመውጣት የእናቱን ብልህ ሐሳብ ይሻል። ሌላኛው ያሉት መጫዎቻዎቹ እጅግ ስላስደሰቱት እናቴ ብታያቸው እንደ እኔ ትደሰታለች ብሎ በማሰብ ወደርሱ እንድትመለከት ይፈልጋል። አንድ የአወንታ ቃል ለሰዓታት ልቡ በደስታ እንዲፍነከነክ ያደርገዋል። በነዚህ የከበሩ ትንንሽ ፍጡሮችዋ ላይ እናት ብዙ የብርሃን ጮራና ሐሴት ማሳረፍ ትችላለች። በመገኘትዋ ቤታቸው በዓለም ካሉ ቦታዎች ሁሉ በላይ በብርሃን የፈካ ይሆንላቸው ዘንድ እነዚህን ውድ የአብራኳ ክፋዮች ከልብዋ ጋር ማቆራኘት ትችላለች። ሆኖም የእናትየዋ ትዕግሥት በነዚህ ጥቃቅን ትኩረት የሚያሻቸው በማይመስሉ ፈተናዎች ይሟጠጣል። ዕረፍት-የለሽ እጆቻቸውና ተክለፍላፊ እግሮቻቸው ከባድ ሥራና ግራ መጋባት ይፈጥሩባታል። እራስዋን አጥብቃ መቆጣጠር ይኖርባታል፤AHAmh 168.2
ያለበለዚያ ትዕግሥት-የለሽ ቃላት ከአፏ ያመልጣታል። አሁንም ቅድምም እራስዋን ልትረሳ ምንም አይቀራትም፤ ሆኖም ወደሚያዝንላት አዳኝዋ የምታደርሰው የጥሞና ፀሎት መንፈስዋን ያረጋጋዋል፤ እራስዋን በመቆጣጠር ክብርዋን እንዳስጠበቀች በዝምታ ማለፍ ያስችላታል። በተረጋጋ ቅላፄ ትናገራለች፤ ሆኖም ከሻካራ ቃላት ለመታቀብና ቁጡ ስሜትን ለማሸነፍ ብዙ ጉልበት ፈጅታለች። እነዚያ ውጣ ያስቀረቻቸው ቃላት ቢወጡ ኖሮ በልጆችዋ ላይ ያላትን ተጽዕኖ በማበላሸት ለመመለስና ለማስተካከል ብዙ ጊዜ ይወስድባት ነበር።AHAmh 168.3
ልጆች የመለየት ችሎታቸው ፈጣን ነው፤ ታጋሽና አፍቃሪ የሆነን ድምጽ የመውደድንና የፍቅርን ጠል ከልባቸው ከሚያደርቀው ከብስጩና ፈርጠም ያለ ትዕዛዝ ለይተው ያውቃሉ። እውነተኛ ክርስቲያን እናት ሩኅሩኅ ፍቅር በመንፈግ በብስጪት ልጆችዋን ከፊትዋ አታባርርም። AHAmh 168.4
አዕምሮን መልክ ማስያዝና ባህርይን መቅረፅ፦ የተለየ ኃላፊነት በእናት ላይ አርፏል። በደም ሥርዋ የሚመገበውና የአካል ግዝሙ የሚሠራበትን እንዲሁም አዕምሮውንና ባህርይውን የመቅረጽ አካላዊና መንፈሳዊ ተጽዕኖ ታካፍለዋለች። በእምነት ጠንካራ የነበረችው ዮካቤድ “የንጉሡን ትዕዛዝ ሳትፈራ” ሙሴን ወለደች እርሱም የእስራኤል ታዳጊም ሆነ። እራስዋን የካደችው ሰማያዊ ብርታት የነበራት የፀሎት ሴት ሐና የሰማይ-እዝ የሆነውን ልጅ፣ የማይደለለውን ፈራጅ፣ የእስራኤልን ቅዱስ ትምህርት ቤቶች ያቋቋመውን ሳሙኤልን ወለደች። ከዘመዷና ከናዝሬትዋ ማርያም ጋር ተመሳሳይ ሐሳብ የነበራት ኤልሳቤጥ የመሲሁ አዋጅ ነጋሪ እናት ነበረች። AHAmh 168.5
የዓለም ባለዕዳነት ለእናቶች፦ እቅዳቸውን ለማሳካት ደፋር የሆኑ፤ በችግርና በፈተና መሐል ከቆሙበት ፈቀቅ የማይሉ፤ ለእውነትና ለለውጥ ጠበቃ በመቆም ፍንክች የማይሉ፤ የላቀውንና የተቀደሰውን የእውነት ፈለግ በመከተል ዓለማዊ ክብራቸውንናሕይወታቸውን ጭምር ለእግዚአብሔር ክብር አሳልፈው የሰጡ ወንዶችን ላበረከቱ፤ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ለሚመላለሱ እናቶች ዓለም ምን ያህል ባለ ዕዳ እንደሆነች በጌታ ቀን የሚታይ ይሆናል። AHAmh 169.1
እናቶች ሆይ የእናንተ ተጽዕኖና ተምሣሌትነት የልጆቻችሁን ባህርይና እጣ ፈንታ እንደሚነካ ተገንዘቡ፤ ከኃላፊነታችሁም አንጻር እውነቱን፣ መልካሙንና ውቡን ብቻ የሚያንፀባርቅ ሚዛናዊ ህሊናና ንጹህ ባህርይ አዳብሩ። AHAmh 169.2